የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ቦታ ተረክበው ባላለሙ 459 ባለሃብቶች ላይ እርምጃወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ቦታ ተረክበው ባላለሙ 459 ባለሃብቶች ላይ እርምጃወሰደ
ባህር ዳር፤ መጋቢት 22 ቀን 2015(ኢዜአ) ፡- የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ቦታ ተረክበው ባላለሙ 459 ባለሃብቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።
የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ይሄነው አለም፤ በክልሉ እያደገ የመጣውን የኢንቨስትመንት ፍሰት በሕግና ስርዓት መምራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ይህም በክልሉ የኢንዱስትሪ፣ የግብርናና የአገልግሎት ኢንቨስትመንት ዘርፎችን በአግባቡ በመምራት ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካትና ለስራ እድል ፈጠራ ለማዋል እየተደረገ ላለው እንቅስቃሴ ምቹ እንደሆነ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት 459 ባለሃብቶች ለኢንቨስትመንት ቦታ ወስደው የተሰጣቸውን ቦታ አጥረው በማስቀመጣቸው እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።
እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል 72 ባለሃብቶች የተረከቡትን 278 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በቀሪዎቹ 387 ባለሃብቶች ላይ ደግሞ እንደየ ችግራቸው መጠንና ከውላቸው ያሳለፉትን ጊዜ ከግምት ውስጥ በማስገባት ድጋፍና ክትትል ተደርጎላቸው ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
በማስጠንቀቂያው መሰረትም ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ግንባታ በመግባትና ወደ ማምረት መሸጋገር እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
በባህርዳር ከተማ ከኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒሰን የምግብ ዘይት ፋብሪካ ባለቤት አቶ ይልቃል ካሴ ፤ ፋብሪካውን ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ሶስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውሰጥ ገንብቶ በማጠናቀቅ ታህሳስ ወር 2015 ዓ.ም ወደ ማምረት መሸጋገሩን ገልጸዋል።
ፋብሪካው በቀን ከ30 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት እንዲሁም ለእንስሳት መኖና ሌሎች ተያያዥ ምርቶችን በማምረት ወደ ገበያ እያቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ግንባታው ከተያዘለት ጊዜ አስቀድሞ በማጠናቀቅ እየጨመረ ካለው የግንባታና የፋብሪካ ቁሳቁስ ዋጋ ወጪ መዳን መቻላቸውን አስረድተየዋል።
በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ለጠየቁ ከ344 ቢሊየን ብር በላይ ሃብት ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል።