ድሬዳዋ ቀድሞ ወደነበረችበት የኢትዮጵያ የንግድ ማዕከልነቷ እየተመለሰች ነው - ከንቲባ ከድር ጁሀር - ኢዜአ አማርኛ
ድሬዳዋ ቀድሞ ወደነበረችበት የኢትዮጵያ የንግድ ማዕከልነቷ እየተመለሰች ነው - ከንቲባ ከድር ጁሀር
አዲስ አበባ መጋቢት 22/ 2015 (ኢዜአ) ድሬዳዋ ከለውጡ በኋላ መሰረት ልማት በማስፋፋት ቀድሞ ወደነበረችበት የኢትዮጵያ ንግድ ማዕከልነቷ እየተመለሰች መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር ገለጹ፡፡
የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የለውጡ አመራር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከተማዋን ወደ ቀድሞ የንግድ ኮሪደርነቷ መልሷታል ብለዋል፡፡
የደረቅ ወደብ ስራ መጀመሩና ነፃ ንግድ ቀጣና መከፈት፤ ከተማዋ እንድትነቃቃ አምራቾች ወደ ከተማዋ በስፋት እንዲገቡ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
የቀድሞው የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር የድሬዳዋ_"ደወሌ" በሚል በከተማ አስተዳደሩ ስር እንዲዋቀር በመደረጉ ለድሬዳዋ አስተዳደር ተጨማሪ አቅም ይዞ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡
በመሰረተ ልማት ዘርፍ በተያዘው ዓመት 17 ሺህ አባወራዎች ለቤቶች ግንባታ እንዲቆጥቡ በማድረግ 10 ሺህ ቤቶች ለመገንባት መታቀዱን ገልጸዋል።
መሰረት ልማት በማስፋፋትና ሰላምን በማረጋገጥ ድሬዳዋን የኢትዮጵያ ሁነኛ የንግድ ማዕከልና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ኮሪደር እናደርጋታለን ነው ያሉት፡፡
በከተማዋ ተቀዛቅዘው የቆዩትን የአንድነትና የመተባበር እሴቶችን ለመመለስ ከወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና ነዋሪዎች ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ የወንዝ ዳርቻዎችን በግንብ የማጠር፣ የአፈርና ውሃ ጥብቃ ስራ እንዲሁም እርከኖች እንዲሰሩ መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ኢብራሒም የሱፍ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ፤ ውስብስብ አገራዊ ችግሮችን በመፍታት ለአዲስ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት አኑሯል ብለዋል፡፡
'ትንሿ' ኢትዮጵያ በሚል የምትታወቀው ድሬዳዋ ከለውጡ በፊት በነበረው ስርዓት የተፈጠሩ ችግሮች ከለውጡ ማግስት ለግጭት መንስኤ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በድሬዳዋ አስተዳደር ብሔርና ኃይማኖት ተኮር ግጭቶችን ለመፍታት ብልጽግና ፓርቲ ይዞት በመጣው አዲስ እሳቤ ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
ከለውጡ ወዲህ የአመራሩ የቃልና የተግባር አንድነት በመያዝ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ የሰላምና ፀጥታ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና መሰረተ ልማት ግንባታ የነበረውን ኢ-ፍትሃዊ አሰራር ማስወገድ ተችሏል ብለዋል፡፡
በድሬዳዋ የተደረገው የተቋማት ሪፎርም፤ የንግድ እንቅስቃሴና ህዝባዊ ውይይት አብሮነትን በማጎልበት የፍቅር ከተማነቷን መመለስ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ይዞት የመጣው ሁሉን አሳታፊ አገራዊ እሳቤ የብሔር ብሔረሰቦች መገኛ ለሆነችው ድሬዳዋ ትልቅ ብስራት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡