በመደመር ጽንሰ ሀሳብ ታንጸን የአካባቢውን ሠላም አጠናክረን ማስቀጠል አለብን - አቶ አሻድሊ ሃሰን

204

አሶሳ  መጋቢት 22/ 2015  (ኢዜአ)  በመደመር ጽንሰ ሀሳብ በመታነጽ የአካባቢውን ሠላም አጠናክረን ማስቀጠል አለብን ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተጻፈው የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ለአንባቢያን ተደራሽ የማድረግ መርሃ ግብር ዛሬ በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የመጽሐፍ ሽያጭ መርሀ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አሻድሊ ሃሰን እንዳሉት ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደ ሀገርም ሆን እንደ ክልል ፈታኝ ሁኔታዎች ገጥመው አልፈዋል። 

ይሁንና በተባበረ ክንድ ፈተናዎችን በፅናት በማለፍ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ከፍታ ለማምጣት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

"ይህን ሀገራዊ የከፍታ ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል ከመደመር ትውልድ ብዙ ይጠበቃል" ያሉት አቶ አሻድሊ፣ "የአሁኑ ትውልድ የተጣለበትን ሃላፊነት በስኬት በመወጣት ኢትዮጵያን እንደሚያሻግር አምናለሁ" ብለዋል። 

ለእዚህም በመደመር ጽንሰ ሃሳብ ታንጸን የአካባቢአችንን ሠላም አጠናክሮ ማስቀጠል ዋነኛ ትኩረት ሊሆን ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል። 


 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመደመር ጽንሰ ሃሳብ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ መጽሀፍ በማሳተም ሃገር የመምራት ሃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸው፣ መጽሀፉ ዛሬአችንን እና ነገን ለማሳመር የሚያስችሉ የመፍትሄ ሃሳቦች የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል። 

ከመጽሀፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በክልሉ ደረጃውን የጠበቀ የባህል ሙዚየም ለማስገንባት እንደሚውልም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

ጽህፈት ቤታቸው የ10 ሚሊዮን ብር የመጽሀፍ ግዥ እንደሚፈጽምም ቃል ገብተዋል።

በዝግጅቱ የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስን ጨምር በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች፣ ወርቅ፣ እምነበረድ እና ማዕድን አምራቾች መታደማቸው ታውቋል።

በዝግጅቱ የተሳተፉት ባለሃብቶች በሚሊዮን ብሮች የመጽሀፍ ግዥ ለመፈጸም ቃል እየገቡ ይገኛሉ። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም