ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖን በመቋቋም የአገርን አንድነት ያስቀጠሉ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን አከናውናለች - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

210

አዲስ አበባ መጋቢት 22/2015 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ዓለም አቀፍ ተጽዕኖን በመቋቋም የአገርን አንድነት ያስቀጠሉ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ማከናወኗን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት የነበራትን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ አብራርተዋል።

በእነዚህ ዓመታት በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ የተከሰቱ ችግሮችን በመቋቋም የአገር ሉዓላዊነትን የሚያስቀጥሉ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ማከናወን መቻሉን ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ ፈተና ውስጥ በገባችበት ወቅት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ጎን መቆማቸው፣ የፓርላማ ዲፕሎማሲ፣ የአገርን ጥቅም ማዕከል ያደረጉ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ተጽዕኖን ተቋቁሞ ለማለፍ ከተሰሩ ተግባራት ውስጥ ይጠቀሳሉ።

በተለይም ዓለም አቀፉ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የምጣኔ ሃብት ቀውስ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት የነበረውን ተጽዕኖና ሌሎችን በመቋቋም የአገርን ጥቅም ያስቀጠሉ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል። 

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገርን ጥቅም የሚያስጠብቁ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራዎች በፓርላማ ዲፕሎማሲና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን በመጣበት ወቅት አገር በተለያየ አቅጣጫ ችግር ውስጥ እንደነበረች አውስተዋል።

ለችግሮች ምላሽ በመስጠት ውስንነቶች ቢኖሩም የተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ክስተቶችን በማለፍ አገርን ማስቀጠል መቻሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ነው የገለጹት።

እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ በፓርላማ ዲፕሎማሲ በኩል ከአፍሪካ እንዲሁም ከዓለም አገራትና ሕዝቦች ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እየተሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በማስተዋወቅ የአገርን ምጣኔ ሃብትና ፖለቲካዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ሌሎች በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ያላቸውን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም