የኢትዮጵያን  ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉም አካላት የድርሻውን  መወጣት አለበት - የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን 

396

ባህርዳር፤ መጋቢት 22 /2015(ኢዜአ) ፡- በነበረው ግጭት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ በማቋቋም  በሀገሪቱ  ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ሁሉም አካል የድርሻውን መወጣት እንዳለበት  የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አመለከተ።  

ኮሚሽኑ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በባህርዳር ከተማ ምክክር  እያካሄደ ነው።

በመድረኩ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር  አምባሳደር ተሾመ ቶጋ  እንዳሉት፤የሰሜኑ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር መፍታት መቻሉ እንደ ሃገር ትልቅ ስኬት ነው።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት በሁሉም አካባቢ በይቅርታ ላይ የተመሰረተ ሰላም ለማስፈን ግንባር ቀደም ሚና በመውሰድ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የተጀመሩ የሰላም አማራጭ መንገዶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና በግጭቱ  የተጎዱ ወገኖችን  መልሶ በማቋቋም ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀንበር በበኩላቸው ፤የተፈጠረው ችግር በሰላማዊ መንገድ መፈታቱ  ከማንም በላይ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

የዛሬው ምክክርም ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ህዝቡ ከስጋት ነፃ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል ይሆናል ብለን እንጠብቃለን ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ክሊፈስ ቶሮሪ በበኩላቸው ፤ መንግስት የሀገሪቱን አንድነት ለማፅናት ቅድሚያ ለሰላም ሰጥቶ መስራቱ የሚደገፍ ነው ብለዋል።

ዘላቂ ሰላምን በማስፈን በጦርነቱ የተጎዱ አካላትን በመደገፍ፣ ተፈናቃይ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ድርጅቱ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል  አስታውቀዋል።

በምክክር መድረኩ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሚሽኑ አመራሮችና አባላት ሌሎችም  ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም