ቀጥታ፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ስኬታማ ለማድረግ ድጋፋችንን እናጠናክራለን- የሐረር ነዋሪዎች

ሐረር  መጋቢት 22 /2015 (ኢዜአ) ፡- ለታላቁ የኢትዮያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬታማነት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ  በሐረር ከተማ  አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የገንዘብ ቁጠባ ማህበርና የንግድ ማህበረሰብ  አባላት አስታወቁ።

በሐረሪ ክልል ባለፉት ሦስት ወራት ለግድቡ ግንባታ በተፈጠረው የህዝብ ንቅናቄ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ  መሰብሰቡን የክልሉ  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ  ጽህፈት ቤት ገልጿል።

በከተማው የኮኮብ ሸዋበር የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ኃላፊነቱ የተወሰነ የኅብረት ሥራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ተሾመ በቀለ  እንደገለጹት፤ የግድቡ ግንባታ በስኬት መቀጠሉ የኢትዮጵያውያን ትብብር  ያስገኘውን ውጤት እንደሆነ ያሳያል።

የግድቡ  ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ  የማህበሩ አባላት በነፍስ ወከፍ ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ማህበሩ ከ30ሺህ ብር በላይ ቦንድ ግዢ መፈጸሙን አስታውሰው፤ አሁንም የ40ሺህ ብር  ቦንድ ግዢ ማከናወናቸውን  ተናግረዋል። 

በአንድነት ተነሳስተው እያካሄዱት ያለው ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል። 

ኢትዮጵያውያን ከተባበሩና ለጋራ ዓላማ በአንድነት ከቆሙ ታሪክ መስራት እንደሚችሉ ግድቡ ትክክለኛ ማሳያ መሆኑን  በከተማው በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ሥራ የተሰማራው ወጣት ደጀኔ ፈቀደ  ገልጿል። 

ባለፉት ዓመታት የ12ሺ ብር ቦንድ መግዛቱን ያወሳው ወጣት ደጀኔ፤ የኢትዮጵያን  ብርሃን የሆነው የህዳሴ ግድብ  ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፌን አቀጥላለሁ ብሏል።

በቅመማ ቅመምና በርበሬ ንግድ የተሰማሩት ወይዘሮ መሳይ ግርማ፤ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ  የቦንድ ግዢ ከተጀመረ አንስቶ  የ13ሺ 500 ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም የታላቁ የግድቡ ግንባታ በደረሰበት ደረጃ መደሰታቸውና ስራው  ከፍጻሜ እስኪደርስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

የሐረሪ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤትና በክልሉ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ ፤ በክልሉ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር  ድጋፍ እየተሰባሰበ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች ላይ ላለፉት ሶስት ወራት በተደረገው ጥረት  ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በስጦታና በቦንድ ሽያጭ መሰባሰቡን ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ ከገቢ አሰባሰብ ስራ በተጨማሪ ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

የክልሉ ሕዝብ በጠንካራ የሀገር ፍቅር ስሜት ከዚህ ቀደም የሚያደርገውን ድጋፍና ተሳትፎ እንዲያጠናክር አቶ ሄኖክ ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም