የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ሰው ሰራሽ አስተውሎት በተለያዩ ተቋማት ስራ ላይ እንዲውሉ እየሰራ ነው- የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር

366

አዲስ አበባ መጋቢት 22/2015 (ኢዜአ)፦ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በተለያዩ ተቋማት ስራ ላይ እንዲውሉ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና ገለጹ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን ጎብኝተዋል።

በኢንስቲትዩቱ የተከናወኑ በርካታ ስራዎችን በተመለከተ ዋና ዳይሬክተሩ ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ገለጻ አድርገውላቸዋል። 

ዋና ዳይሬክተሩ በገለጸቸው የደህንነት፣ የጤና፣ የፋይናንስ፣ የትምህርትና ሌሎት አገልግሎቶች የተሳለጡና ጥራታቸውን የጠበቁ ለማድረግ የተለያዩ ሲስተሞች ለምተው ተግባራዊ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል። 

በስማርት ሲቲ ግንባታ በተለያዩ የመዲናዋ አካባቢዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የደህንነት ካሜራዎች ተተክለው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም እንዲሁ።


 

የጤናውን ዘርፍ አገልግሎት ለማዘመን ደግሞ በዘውዲቱ መታሰቢያና በየካቲት 12 ሆስፒታሎች የስኳር በሽታን ልየታና ምርመራ ማደረግ የሚያስችል ሲስተም ለምቶ የሙከራ ትግበራው ተጠናቋል ብለዋል።

የፋይናንስና የትምህርት ዘርፉም በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተደገፈ እንዲሆን ተመሳሳይ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

ዘርፉን በሰው ሃይል ለማጠናከር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር ከተለያዩ አገራት በማስመጣት እንዲያስተምሩ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

በተለያዩ ተቋማት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስራ ላይ እንዲውል ኢንስቲትዩቱ እየሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።


 

የቋሚ ኮሚቴው የመስክ ቡድን አስተባባሪ ፋናዬ መለሰ፤ የኢንስቲቱዩቱ ጅምር ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በተቋማት ጥቅም ላይ ለማዋል የተያዘው እቅድም ሊበረታታ ይገባል ነው ያሉት።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት በኢትዮጵያ ለተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችና የለውጥ ጉዞ አጋዥ መሆኑንም ቋሚ ኮሚቴው በቅጡ ተገንዝቧል ብለዋል።

በመሆኑም የኢንስቲትዩቱን ስራዎች ውጤታማነት ለማስቀጠል ምክር ቤቱ በቀጣይነት እገዛ የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም