የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የብሔራዊ ባንክ ህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪና የገንዘብ ዝውውር ተዋናዮች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ገለጹ

462

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2015(ኢዜአ)፦ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የብሔራዊ ባንክ ህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪና የገንዘብ ዝውውር ተዋናዮችን በጥናት በመለየት ቀጣይ እርምጃ እንደሚወስዱ አስታወቁ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ እንቅስቃሴ ዙሪያ ያካሄደው ሰፋ ያለ ጥናት ዛሬ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

የብሔራዊ ባንክ ገዢ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት፣ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት የሥራ ሃላፊዎች፣ ኮሚሽነሮች እንዲሁም የደኅንነትና የፀጥታ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ የቀረበው ጥናት በዘርፉ ያሉ ችግሮችንና የተለያዩ የውጭ ሀገራትን ተሞክሮዎችም ጭምር በጥልቀት የዳሰሰ ነበር።


 

የጥናቱን ግኝቶች መነሻ በማድረግ ህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬና የገንዘብ ዝውውርን ሰንሰለት ለመበጠስ እንዲሁም የድርጊቱ ተዋናዮች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የፖሊስ፣ የሥርዓትና የተጠያቂነት መፍትሄዎችን የሚጠቁሙ ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል።

በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገባቸውን ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎችንም አመላክቷል።

በጥናቱ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና የውጭ ምንዛሬ ገበያዎች የሀገርን ኢኮኖሚ በማዳከም፣ የኑሮ ውድነትን በማናርና ሙስናን በማስፋፋት ሀገርን ለከፋ አደጋ እያጋለጡ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡

በህገ-ወጥ ተግባራቱ መንግሥታዊና የግል ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የውጭ ሀገር ዜጎች ጭምር የሚሳተፉ መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ፤ ከውጭ ሀገራት እስከ መሀል ሀገር የተዘረጋው ህገ-ወጥ የጥቅም ትስስር በደላሎች፣ በድርጅቶች፣ በኩባንያዎችና በባንክ ሥርዓቱም ጭምር እንደሚደገፍ አመልክቷል።

ይህም በሀገራችን እየታየ ላለው ቅጥ ያጣ የዋጋ ንረትና ማህበራዊ ችግር አንዱ ቁልፍ ምክንያት መሆኑን አሳይቷል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንዳሉት፤ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬ ንግድ የሀገርን ህልውናና የህዝብን ጥቅም እየተፈታተነ ያለ ብሔራዊ አደጋ መሆኑን በመረዳት አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በልዩ ትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡

ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የንግዱ ማህበረሰብና ህዝቡ በትብብርና በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡


 

በጥናቱ የተለዩና ችግሩ በስፋት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች፣ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እርምጃ በቀጣይነት የሚወሰድ መሆኑን ነው የገለፁት።

ህገ-ወጥነትን በመቆጣጠር፣ የሀገርንና የህዝብን ህልውና በመታደግ ትግሉ ውስጥ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የህግ አካላትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ተቀናጅተውና ተናበው ሊሠሩ እንደሚገባም አቶ ተመስገን ጥሩነህ አሳስበዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመቀናጀትና ሌሎች አካላትን በማሳተፍ ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ በትኩረት እንደሚሠራም ጠቁመዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬ ንግድ ባንኩ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በአግባቡ ለማስተዳደር እንዳይችል እንቅፋት ሆነዋል፣ ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታትም ጥረት እየተደረገ ነው።


 

የውጭ ምንዛሬ ብቻ ሳይሆን የብር እንቅስቃሴውም ከባንክ ሥርዓት ውጭ በመዘዋወር ላልተፈለገ ዓላማ እየዋለ መሆኑ ተደርሶበታል ያሉት አቶ ማሞ በርካታ የብር ኖቶችን ከባንክ ሥርዓት ውጭ በማንቀሳቀስ ላልተፈለገ ዓላማ በሚያውሉ ወንጀለኞች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

በቀረበው ጥናት ላይ ውይይት ያደረጉ የብሄራዊ ባንክ ገዢን ጨምሮ የመድረኩ ተሳታፊዎች የቀረበው ጥናት አጠቃለይ ችግሩን፣ የችግሩን ተዋንያን እና የመፍትሄ ሐሳቦችን በሚገባ ያመላከተ በመሆኑ ለአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ምስጋና ማቅረባቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኅን በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም