የኢጋድ ዋና ፀሀፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል እና ለጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ዕውቅናና ሽልማት አበረከቱ

344

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2015(ኢዜአ)፦የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን/ኢጋድ ዋና ፀሀፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል እና ለጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ዕውቅናና ሽልማት አበረከቱ።

ዶክተር ወርቅነህ ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና ለጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ኃይል ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል አብዱራህማን አሊ ካህን ዕውቅናና ሽልማት ሰጥተዋል።


 

ዶክተር ወርቅነህ ዕውቅናና ሽልማቱ ያበረከቱት ሁለቱ ከፍተኛ አመራሮች የሁለቱን ፖሊስ ተቋማት በማስተባበር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በቀጠናው የሚስተዋለውን የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ላበረከቱት አስተዋጽኦ መሆኑ ተገልጿል።


 

በተጨማሪም በህገ-ወጥ የሰዎች፣ የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ እንዲሁም አሸባሪዎችን፣ የፀረ-ሰላም እንቅስቃሴዎችንና የጸጥታ ስጋቶችን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት ሊሆን በሚችል መልኩ የጋራ ግብረ-ኃይል በማቋቋም የድንበር ደህንነት ለመቆጣጠር የላቀ ሚና ስላበረከቱ እንደሆነም ታውቋል።


 

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና የጅቡቲ ብሄራዊ ፖሊስ የጋራ ግብረ ኃይል የድንበር ደህንነትን በጋራ ለመጠበቅ የቴክኒክ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማሟላት የሚያስችላቸውን ዝክረ-ሀሳብ ለኢጋድ ስራ አስፈፃሚ ያቀረቡ ሲሆን ዋና ፀሀፊ ዶክተር ወርቅነህም በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ግብረ ኃይሉን ለመደገፍ ቃል ገብተዋል።

በቀጣይ ሁለቱ የፖሊስ ተቋማት ያቋቋሙትን የጋራ ግብረ-ኃይል የበለጠ በማጠናከር በአፍሪካ ቀንድ የድንበር ደህንነትን ለማረጋገጥ በላቀ ተነሳሽነትና ትብብር እንደሚሰሩ ቃልገብተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም