ኢዜአ በአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ ለመሆን የጀመረውን ተቋማዊ ሪፎርም አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ

447

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአፍሪካ ቀዳሚና ተፅዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ ለመሆን የጀመረውን ተቋማዊ ሪፎርም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የአሐዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለጋዜጠኞቹ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በአግባቡ ተገንዝቦ ሙያዊ ዘገባ መስራት የሚያስችል ለሶስት ቀናት የሚቆይ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።


 

የአሐዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ለጋዜጠኞቹ ሙያዊ ልምዱንና የዘገባ ንድፈሀሳቦችን ለጋዜጠኞች አጋርቷል።

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በኢትዮጵያ የሚዲያ ተቋም ታሪክ ውስጥ አንጋፋ ስም ያለው ተቋም መሆኑን አውስቷል።

የዜና አገልግሎቱ ከኢትዮጵያ አልፎ በቅኝ ግዛት ዘመን ድምፅ አልባ ለነበሩ አፍሪካውያን ድምፅ በመሆን ለነጻነታቸው እንዲታገሉ መረጃዎችን ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሷል።

በአፍሪካ ቀዳሚው የዜና አገልግሎት የሆነው ኢዜአ፤ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሪዎችን እና የነጻነት ታጋዮችን ታሪክ በመሰነድም ኢትዮጵያን በጉልህ ማስጠራቱን ጠቅሷል።

ጋዜጠኛ ጥበቡ እንደሚለው በአፍሪካ ትልቅ ታሪክ እና ስም ያለው ይህ የዜና አገልግሎት በአህጉሪቱ ወደነበረበት ከፍታ እንዲመጣ መስራት ይጠበቅበታል።

አገልግሎቱ በአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ ለመሆን በቴክኖሎጂ፣ በቁሳቁስ፣ በሰው ኃይልና በሌሎች መስኮች የጀመረውን ሁለንተናዊ ተቋማዊ ማሻሻያ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መክሯል።

ለአገልግሎቱ ቀጣይ ስራ መሳካት አመራሩና ጋዜጠኞቹ ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝቧል።

ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ጋዜጠኝነት ሁሌም እየተማሩ የሚኖሩት ስራ በመሆኑ በየጊዜው ለዘጋቢዎች የስራ ላይ ስልጠና መሰጠቱም ባለሙያዎችን የሚያነቃቃ መሆኑን ጠቁሟል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነትና የስትራቴጂክ አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ወንዲራድ ኢዜአ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት የአቅም ግንባታ ስራ ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም ብሔራዊ መግባባትና አገራዊ ገጽታን በመገንባት  እንዲሁም የመረጃ ምንጭነቱን አጠናክሮ መቀጠል የሚያስችል ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በስልጠናው የተሳተፉ የኢዜአ ጋዜጠኞች በበኩላቸው ስልጠናው ለቀጣይ ስራዎቻቸው ተጨማሪ እውቀት የሚገበዩበት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢዜአ ለሌሎች መገናኛ ብዙሃን የዜና ምንጭ በመሆኑ ጥራት ያለውና አስተማማኝ መረጃ ለማድረስ በየወቅቱ አቅማቸውን የሚያሳድጉ መሰል ስልጠናዎች መሰጠታቸው ተገቢ ነው ብለዋል።


 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም