በግለሰብ ቤት የተከማቸ የተበላሸ ቴምር ከወንጀሉ ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን ፖሊስ ገለጸ

436

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2015(ኢዜአ)፦ በግለሰብ ቤት የተከማቸና ለገበያ ሊቀርብ የተዘጋጀ ንፅህናውን ያልጠበቀና የተበላሸ በርካታ ቴምር ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

ተጠርጣሪዎቹ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉት መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ/ም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው ታይዋን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ የግለሰብ መኖሪያ ግቢ ውስጥ መሆኑን ፖሊስ አመልክቷል።

ግለሰቦቹ በመኖሪያ ግቢያቸው በሚገኝ መጋዘን ውስጥ የተበላሸና በጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል በርካታ ቴምር ንጽህና በጎደለው ሁኔታ አስቀምጠው ለአትራፊ ነጋዴዎች በፌስታል አሽገው የ92ሺህ ብር ከሸጡላቸው በኋላ የተበላሸ መሆኑን የተገነዘቡት ገዢዎቹ ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ መሰረት ሊያዙ ችለዋል፡፡


 

መረጃው የደረሰው በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የእፎይታ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያም ከፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማወጣትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ግቢ መጋዘን ውስጥ ባደረገው ፍተሻ መጥፎ ጠረን ያለው የተበላሸ በርካታ ቴምር ተከማችቶ ተገኝቷል።

በክፍለ ከተማው የወረዳ 10 አስተዳደር የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብቱ መካ በበኩላቸው በቁጥጥር ስር የዋለው ቴምር ወደ ህብረተሰቡ ቢሰራጭ በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል።


 

ተበዳዮቹ ከተጠርጣሪዎቹ የገዙትን የተበላሸ ቴምር ለህዝብ ሳይሸጡ እና የግል ጥቅም ሳያጓጓቸው ለሰዎች ጤና በማሰብ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠታቸው ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል፡፡

በቁጥጥር ስር በዋሉት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ ጊዜና ወቅትን እየጠበቁ ህገ-ወጥ ተግባር የሚፈፅሙ ነጋዴዎችም ሆኑ ሌሎች ግለሰቦች ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ ተገንዝበው ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም