በሲዳማ ክልል ያሉ የቱሪስት መስህቦችን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል--የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ

384

ሀዋሳ መጋቢት 21/2015(ኢዜአ) በሲዳማ ክልል የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችን ከጎበኙ የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎች 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሀላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ ለኢዜአ እንደገለጹት ገቢው የተገኘው ባለፉት ሰባት ወራት ክልሉን ከጎበኙ 2 ሚሊዮን በላይ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ነው።

ገቢው ከቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች በደረሰኝ የተሰበሰበ ገቢን ጨምሮ ከሆቴልና ሌሎች የቱሪስት አገልግሎቶች የተገኘ መሆኑን አስረድተዋል።

ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተገኘው መረጃ መሰረት ባለፉት ሰባት ወራት ክልሉን ለመጎብኘት ከመጡ ቱሪስቶች መካከል 20ሺህ የሚሆኑት የውጪ ሀገር ጎብኚዎች መሆናቸውን አቶ ጃጎ ገልጸዋል።

ወደ ክልሉ በመደበኛነት ከሚመጡ የሀገር ውሰጥና የውጪ ጎብኚዎች በተጨማሪ በሀዋሳ የሚከናወኑ ሀይማኖታዊ፣ ባህላዊና ህዝባዊ በዓላትን ምክንያት በማድረግ የሚመጡ ጎብኚዎች ለቱሪስት ፍሰቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን አውስተዋል።


 

በክልሉ ያሉትን የተፈጥሮ፣ ታሪካዊና ሰው ሰራሽ የመስህብ ስፍራዎችን በጥናት በመለየትና በአራት ማዕከል በማደራጀት ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አቶ ጃጎ አስረድተዋል።

በሀዋሳ ከተማ ማዕከል ስር የሀዋሳ የፍቅር ሀይቅ፣ የዓሳ ገበያ፣ የታቦር ተራራ፣ የወንዶ ገነት የተፈጥሮ ደንና ፍል ውሀን የያዘ የመስህብ ስፍራ እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።

የመስህብ ስፍራዎቹን በድረ-ገጽ በሀገር ውስጥና በውጪ መገናኛ ብዙሀንና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አብዛኞቹ በሀዋሳ ከተማ መገኘታቸው በሌሎች አካባቢዎች ጎብኚዎች እንዳይቆዩ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ይህንን ችግር ለማቃለል በቱሪዝም አገልግሎት ዘርፍና በሆቴል ስራ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ቢሮው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም