የወላይታ ዞን አስተዳደር በአበላ አበያ ወረዳ በጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ሶዶ መጋቢት 21/2015 (ኢዜአ) የወላይታ ዞን አስተዳደር በአበላ አባያ ወረዳ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉ የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ ሚስማር፣ የግድግዳና ማገር እንጨትና ሌሎች ቁሳቁችን ያካተተ ነው።


 

ድጋፉን የወላይታ ዞን ምክር ቤት ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ዮሐንስ በየነ አበላ አባያ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል መና  አስረክበዋል።

ድጋፉ የዞኑ አስተዳደር፣ የወረዳና ከተማ መዋቅሮችን በማስተባበር መሰብሰቡ ተገልጿል።

የተፈናቀሉ ዜጎችን ከጊዜያዊ ሰብአዊ ድጋፍ ባለፈ በዘላቂነት ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ አሊያም ወደ ተሻለ ቦታ በማዛወር ለማቋቋም አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዋና የመንግስት ተጠሪው ገልጸዋል።


 

በዞኑ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘውዱ ሳሙኤል በበኩላቸው ተፈናቃዮች በዘላቂነት ሕይወታቸውን የሚመሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የአበላ አበያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል መና ከቀዬያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በዘላቂነት ቋሚ ቤት እንዲሰራላቸው ቦታ ማመቻቸትን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።



 

ከዞኑ የአስተዳደር መዋቅሮች ለተደረገው ድጋፍም አቶ ሳሙኤል መና ምስጋና አቅርበው የተፈናቀሉ ዜጎች  ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

በአበላ አባያ ወረዳ በሚገኙ ጮካሬ፣ ሰላም ጓድ፣ አባያ ጉርቾና አባያ ማራጫ በሚባሉ አራት ቀበሌዎች የሚገኙ ዜጎች የብላቴ ወንዝ ሙላት ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ምክንያት መፈናቀላቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም