በድሬዳዋ ህብረተሰቡ ከድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ራሱን ለመከላከል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት---ማዕከሉ

ድሬዳዋ መጋቢት 21/2015 (ኢዜአ) በድሬዳዋና ዙሪያዋ እየጣለ ባለው ከፍተኛ ዝናብ የሚከሰት ጎርፍ በሰውና በንብረት ላይ አደጋ እንዳያስከትል ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የምስራቅና መካከለኛ ኦሮሚያ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል አሳሰበ። 

ባለፉት አራት ሳምንታት በድሬዳዋና በዙሪያው በሚገኙ ወረዳዎች እየጣለ ያለው ዝናብ ጎርፍ እያስከተለ ይገኛል።


 

የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ትዕዛዙ ገረመው ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ በድሬደዋና በምስራቅ የአገሪቱ ክፍል በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ መጠናከር ጎርፍ ሊያስከትል ይችላል።

በጎርፍ ምክንያት በሰውና በንብረት ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመከላከል ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ገልጸው፣ በተለይ ከጎርፍ መውረጃ አካባቢዎች በመራቅ ራሱን መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሚመለከታቸው ተቋማትም አደጋውን ቀድሞ መከላከል እንዲቻል ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የለውጥና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ በበኩላቸው ሰሞኑን የጣለው ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ አደጋ አስከትሏል።


 

በተለይ በድሬዳዋ አሸዋ በተባለው የደቻቱ ጎርፍ መውረጃ ስፍራ ላይ ተኝቶ የነበረ አንድ ግለሰብ በጎርፍ ምክንያት ህይወቱ ማለፉን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም በጎርፍ መውረጃው አሸዋ ላይ የነበረውን ልባሽ አልባሳት በጎርፍ ተጠርጎ መውሰዱን ገልጸዋል።

ከአምስት ቀናት በፊትም ከድሬዳዋ ተጎራባች አካባቢዎች ድንገት በቀን የመጣው ጎርፍ በቀፊራ የገበያ አካባቢ የአትክልትና ፍራፍሬ ንብረት መውሰዱን አስታውሰዋል።

እንደኮማንደር ገመቹ ገለፃ አንዳንድ ነዋሪዎች በአሸዋው ላይ የሚያልፈውን ጎርፍ ለማቋረጥ  የሚያደርጉት ሙከራ ለአደጋ እያጋለጠ ይገኛል።

ፖሊስ ከገጠር ቅርንጫፎች ጭምር የደረሰውን መረጃ ለህብረተሰቡ ከማሳወቅ ባለፈ ሰዎች ከቦታው እንዲነሱ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

በቀጣዮቹ ቀናት መሰል ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰቡ የራሱን ጥንቃቄ ከማድረግ ባለፈ በጎርፍ መውረጃ ሥፍራ ላይ የንግድ እንቅስቃሴ ማከናወን እንደሌለበት አሳስበዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር የአደጋ ስጋት አመራር ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዳይሬክተር አቶ አብዱልሰላም ዩሱፍ በበኩላቸው፤ በጉዳዩ ላይ ለህብረተሰብ ግንዛቤ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

"በተለይ የጎርፍ አደጋ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎችና በጎርፍ መውረጃዎች ላይ የሚኖሩና የሚነግዱ ሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

የጎርፍ አደጋን ለመከላከል በድሬዳዋ ገጠር የተሰሩ የግንብና የጎርፍ መውረጃ ቦዮች በአግባቡ እየተጠገኑ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የድሬዳዋ መንገዶች ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ወርቅነህ ናቸው።

ባለስልጣኑ ከድሬዳዋ ሥራ አስኪያጅ ፅህፈት ቤት፣ ከውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፣ ከጽዳትና ውበት ኤጀንሲ እንዲሁም ከድሬዳዋ ግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመቀናጀት የጎርፍ አደጋን የመከላከልና ውሃውን ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የጎርፍ መከላከያ አዲስ ግንቦችን የመገንባትና ነባሮቹን የመጠገን፣ የጎርፍ መውረጃ ትቦዎችን ከደለል የማፅዳት እንዲሁም በገጠር የጎርፍ መውረጃ አካባቢዎች ላይ የድንጋይ ክትሮችና የተፋሰስ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

ጎርፍ የሚፈስበትን ስፍራ ለተለያዩ አገልግሎቶች ማዋል ተገቢ ባለመሆኑ ህብረተሰቡ ራሱን ከዚህ ህገ-ወጥ ድርጊት መቆጠብ እንዳለበትም አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም