የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለፍጻሜ ለማድረስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም ዜጋ ተሳትፎውን ሊያጠናክር ይገባል--የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት

566

ሆሳዕና መጋቢት 21/2015(ኢዜአ)የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለፍጻሜ ለማድረስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም ዜጋ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ተጠየቀ።

ለግድብ ግንባታ የሚሆን ገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር በሆሳዕና ከተማ ተጀምሯል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ መኮንን መንገሻ እንዳሉት በዜጎች የተቀናጀ ርብርብ የተጀመረው የግድቡ ግንባታ በመገባደድ ላይ ይገኛል።

የግድቡን ስራ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ የሁሉንም ህብረተሰብ ጠንካራ ድጋፍና ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።


 

የግድቡ ግንባታ ከፍፃሜ መድረስ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ከማረጋገጥ ባሻገር የግብርና ልማት እንቅስቃሴውን ለማሳለጥና ቱሪዝምን በማስፋፋት ረገድ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች እንዳሉት ገልጸዋል

ለመጪው ትውልድ አሻራ ለማኖርና የሀገሪቱን ፈጣን እድገት ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ስላለው ህብረተሰቡ እስካሁን ሲያደርግ የነበረውን ተሳትፎ በማጎልበት ግድቡን ለስኬት እንዲያበቃ ተወካዩ ጥሪ አቅርበዋል።

በደቡብ ክልል የታላቁ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚልክያስ እስራኤል በበኩላቸው ግድቡ የተለያዩ ተግዳሮቶችን ተሻግሮ የመጨረሻው ምእራፍ ላይ መድረሱን አንስተው፤ ለዚህም ህዝቡና መንግሥት የጎላ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ተናግረዋል።


 

በደቡብ ክልል የሀዲያ ዞን ህዝብ እስካሁን ለግድቡ 100 ሚሊዮን 613ሺህ ብር በቦንድ ግዥና በድጋፍ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውሰው፤ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል።

“ግድቡ የአሁኑ ትውልድ አሻራ የመጪው ትውልድ ቅርስ” ነው ያሉት 50ሺህ ብር ድጋፍ ያበረከቱት የሆሳዕና ከተማ ነዋሪው አቶ ደበበ ኤርመኮ ግድቡ እዚህ ደረጃ ላይ በመድረሱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል

ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤቱ በከተማው ዛሬ በነበረው ቆይታ የቦንድ ሽያጭን ጨምሮ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ያካሄደ ሲሆን በፕሮግራሙ ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም