በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና በህዝቡ ትብብር እየተገነቡ ያሉ ተቋማት የሕብረተሰቡን ተሳትፎ እንደሚያሳድጉ ተገለጸ

236

ድሬደዋ መጋቢት 21/2015 (ኢዜአ)፦በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና በህዝቡ ትብብር እየተገነቡ ያሉ የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሕብረተሰቡን ተሳትፎ በእጅጉ ሊያሳድጉ የሚችሉ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን ያዘጋጁት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ቡድን ጉብኝት ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።


 

በዛሬው እለት የድሬዳዋ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ የድሬዳዋ ስታዲየም ማሻሻያ ፕሮጀክት፣ የድሬዳዋ ደወሌ ምድር ባቡር ድርጅት እና የሳቢያን አጠቃላይ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት ማዕከል ተጎብኝተዋል፡፡

ከጉብኝቱ መዳረሻዎች መካከል በ9ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውንና በ307 ሚሊዮን ብር እየተገነባ ያለው የድሬዳዋ ስፖርት አካዳሚ አንዱ ነው።

ዓለም አቀፍ ደረጃን ባሟላ መልኩ እየተገነባ የሚገኘው የድሬዳዋ ስፖርት አካዳሚ የወጣቶችን ሰብእናና አካል ብቃት ለመገንባት ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

የኦሎምፒክ መወዳደሪያ መስፈርትን ጠብቆ እየተገነባ የሚገኘው ብቸኛው የቤት ውስጥ መዋኛ የሚገኘውም እዚሁ አካዳሚ ውስጥ ነው።


 

በተመሳሳይ በድሬዳዋ ስታዲየም የማሻያያ ፕሮጀክት ሥራ የስታዲየም ሥራው ተጠናቆ በቀጣዩ ዓመት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ብቁ እንዲሆን የአርቴፊሻል ሳር የማልበስ ስራ በቅርቡ እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡

የድሬዳዋ ምድር ባቡር በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ቡድኑ የተጎበኘው ሌላው ተቋም ነው።

የ127 ዓመታት እድሜ ያለው አንጋፋው ተቋም ለ25 ዓመታት ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ ቢቆይም በ2014 ዓ.ም መንግስት በከተማ አስተዳደሩ እንዲተዳደር በፈቀደው መሰረት በጥቂት ወራት ውስጥ ሶስት ባቡሮችን ጠግኖ ወደ ሥራ አስገብቷል።

በቀጣዮቹ ወራትም ተጨማሪ ባቡሮችን በመጠገን በአመቱ መጨረሻ ሰባት ባቡሮችን ወደ ስራ የማስገባት እቅድ እንዳለው በጉብኝቱ ተገልጿል።


 

ሌላው በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ቡድኑ የተጎበኘው በሳቢያን አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ ተገንብቶ የተጠናቀቀውና በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር የተገለጸው የኩላሊት ሕመምተኞች የዲያሊሲስ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ነው።

ማዕከሉ በድሬዳዋ ብሄራዊ ሲሚንቶ ፋብሪካና በከተማው ወጣቶች ተሳትፎ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሕንጻ ግንባታው ተጠናቋል።

በአንድ የከተማው ነዋሪ በጎ ፈቃደኛ ልገሳ ደግሞ 10 የዲያሊሲስ ማሽኖች ተገዝተው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል።

በዚህም ማዕከሉ በቅርቡ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀመርና በከተማው በአንድ የግል ሆስፒታል ብቻ እየተሰጠ ያለውን የዲያሊሲስ አገልግሎት እጥረት እንደሚፈታም ታምኖበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም