በወንጀል ተጠርጥረው ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ የህወሃት ሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች ክስ መቋረጡን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2015(ኢዜአ)፦በወንጀል ተጠርጥረው ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ የህወሓት ሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮች ክስ መቋረጡን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በፌዴራል መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት ከግጭቱ ጋር ተያያዥ የሆኑ ወንጀሎች ተጠያቂነት በተመለከተ ያለውን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ ሊታዩ እንደሚገባ ስምምነት ላይ መደረሱን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

በዚህ መሰረትም በወንጀል ተጠርጥረው ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ የህወሃት ሲቪልና ወታደራዊ አመራሮችን ክስ በማቋረጥ ጉዳያቸው በቀጣይ በሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ እንዲታይ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የፍትህ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ አመላክቷል።

ስለዚህም በተገለፀው አግባብ ከዚህ ጋር በተያያዘ ክስ ቀርቦባቸው በክርክር ሂደት ላይ ይገኙ የነበሩ የወንጀል ክሶች በአዋጅ 943/2008 አንቀጽ 6 (3) (ሠ) መሰረት ክሳቸው የተነሳ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም