በዲላ ከተማ 7ሺህ 935 ነዋሪዎች በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ወደ ስራ መግባታቸው ተገለጸ

313

ዲላ መጋቢት 21/2015 (ኢዜአ) በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ 7ሺህ 935 የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው ነዋሪዎች በሰፍቲኔት ፕሮግራም  ወደ ሥራ መግባታቸውን የከተማው ሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በፕሮግራሙ በተፈጠረላቸው የሥራ እድል ኑሯቸውንና የከተማውን ገጽታ ለመለወጥ እንደሚተጉ ተጠቃሚዎቹ ገልጸዋል።

የከተማው ሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽህፈት ቤት በበኩሉ፤ ፕሮግራሙ የነዋሪዎችን የምግብ ዋስትና ችግር ከማቃለል ባለፈ የከተማውን ልማትና ዕድገት ከማገዝ አንጻር ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን አመልክቷል።


 

የጽህፈት ቤቱ ሐላፊ አቶ እድሉ ታደሰ የኢትዮጵያ መንግስትና የዓለም ባንክ ባወጡት መሰፈርት መሰረት የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው 7ሺህ 935 ነዋሪዎች የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ሆነዋል።

"ተጠቃሚዎቹ በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ በተፋሰስ ልማትና በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር እንዲሁም በአነስተኛ መሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች በመሳተፍ ኑሯቸውን የሚደግሙ ይሆናል" ብለዋል።

ለቀጣይ ሶስት ዓመታት ለሚካሄደው ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ከኢትዮጵያ መንግስትና ከዓለም ባንክ 58 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ጠቅሰዋል።


 

ተጠቃሚዎቹ ቆይታቸው ሲጠናቀቅ ወደ ቀደሞ ሕይወታቸው እንዳይመለሱ በየወሩ በሚቆጥቡት ገንዘብ ላይ ተጨማሪ ሀብት በማከል ወደ ተሻለ የሥራ መስክ የሚሰማሩበት የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱን ሐላፊው አስታውቀዋል።

"የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው ወገኖች ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ወደ  ሚደጉሙበት ሥራ መግባታቸው ለነዋሪውና ለከተማው ልማት ጠቀሜታው ድርብ ነው" ያሉት ደግሞ የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተስፋጽዮን ዳካ ናቸው።

በተለይ በከተማው ስር የሰደደ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን ችግር ከማቃለል ባለፍ ለማህበራዊ ለውጥ በተለይ በልጆች ትምህርትና ጤና ላይ መሻሻል ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ተጠቃሚዎች እድሉን በመጠቀም የሚያገኙትን ገቢ በመቆጠብና በአግባቡ በመጠቀም ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ለሌሎች ማስተማር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ተጠቃሚዎች በበኩላቸው በተሰማሩት የስራ መስክ ጠንከረው በመስራት ከራሳቸው አልፈው ለከተማው ልማት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል ወይዘሮ አይናለም አለሙ እንደገለጹት፤ መንግስት የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉ  ችግራቸውን እንደሚያቃልልላቸው ገልጸዋል።

በተሰማሩበት የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥራ ጠንከረው በመሥራት ኑሯቸውንና  የከተማውን ገጽታ ለመቀየር ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል።


 

ባለባቸው የአቅም ችግር ልጆቻቸውን ለማስተማር ይቸገሩ እንደነበር ያነሱት ደግሞ ወይዘሮ ፋጤ የሱፍ ናቸው።

መንግስት ችግራቸውን ተረድቶ የሥራ እድል ተጠቃሚ ስላደረጋቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ ያገኙትን እድል በአግባቡ በመጠቀም ኑሯቸውን ለማሻሻልና ከተማቸውን ለመለወጥ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

በከተማው የዛሬዎቹን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት 10ሺህ በላይ ነዋሪዎች በልማታዊ ሴፍቲኔት መርሐ-ግብር ወደ ሥራ በመግባት ተጠቃሚ መሆናቸውን ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም