12 የመደመር ትውልድ የመዝናኛና የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት በመጪው ሰኔ ወር ለአገልግሎት ይበቃሉ-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2015 (ኢዜአ) በመዲናዋ ከ “መደመር ትውልድ” መጽሐፍ ሽያጭ በሚገኝ ገቢ የሚገነቡት 12 የሕጻናትና ወጣቶች የመጫወቻና የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት ግንባታቸው በመጪው ሰኔ ወር ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚጀምሩ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በአዲስ አበባ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የስፖርት ማዘውተሪያና የመጫወቻ ማዕከል ግንባታ የማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ዛሬ ተከናውኗል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ቆሼ አካባቢ ቴኒስ ሜዳ፣ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ፈረንሳይ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳና በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት የስፖርት ማዘውተሪያና የመጫወቻ ማዕከላት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

ከንቲባዋ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ከ“መደመር ትውልድ” መጽሐፍ የሚገኘው ገቢ ለወጣቶችና ሕጻናት የመዝናኛ ስፍራዎችን ለመገንባት እንዲውል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መፅሐፉን በስጦታ ማበርከታቸውን አስታውሰዋል፡፡

መጽሐፉ ትውልድ ቀረጻ ላይ ያተኮረ መሆኑን ያነሱት ከንቲባዋ፤ ሽያጩ የሚካሄደውም በሚሰበሰበው ገቢ ትውልድ የሚቀረፅባቸውን ማዕከላት ለመገንባት ነው ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም 12 የመደመር ትውልድ የስፖርት ማዘውተሪያና የመጫወቻ ማዕከላት ግንባታ መጀመሩን ጠቅሰው፤ በመጪው ሰኔ ወር ግንባታቸው እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።

ያለፉት ትውልዶች በዘመናቸው ከፈጸሟቸው መልካም ተግባራትና ጉድለቶች የተሻለች ሀገር የሚገነባ ትውልድ ለመፍጠር ሃሳብና ምቹ ስፍራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በአእምሮና በአካል የዳበረ ሀገሩን የሚወድ ጠንካራ ትውልድ ለመገንባት በተጀመረው ፕሮጀክት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንባታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም በመደመር እሳቤ በሀገሩ የሚኮራ እና ህብረ ብሔራዊ አንድነቱን የሚያስጠብቅ ትውልድ ለማፍራት ከአምስት ሺህ ያላነሱ የስፖርት እና የመዝናኛ ስፍራዎችን እንሰራለን ብለዋል፡፡

ለልጆች የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት እንዲሁም በስፖርትና ሥነ-ምግባር የተካኑ የነገ ሀገር ተረካቢዎችን ለማፍራት ሁሉም በትኩረት እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ በላይ ደጀን በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት የከተማ አስተዳደሩ በሰጠው ትኩረት 235 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተገንበተው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቹም የፋት-ሳል፣ እግር ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ቮሊቦልና ጠረጴዛ ቴኒስን ያካተቱ ናቸው ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም