መንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በመልሶ ግንባታ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው-የመከላከያ ሚኒስትር ዲኤታ ማርታ ሉዊጂ

633

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2015(ኢዜአ)፦መንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በመልሶ ግንባታ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ዲኤታ ማርታ ሉዊጂ ገለጹ።

በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት "ድህረ-ግጭት መልሶ ማቋቋምና የሰላም ግንባታ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም" በሚል አገር አቀፍ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው።


 

የመከላከያ ሚኒስትር ዲኤታዋ ማርታ ሉዊጂ በዚሁ ወቅት መንግስት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማቋቋም፣ የሽግግር ፍትህና ሌሎች የዘላቂ ሰላም ማሳለጫ መንገዶችን በመዘርጋት ለሁለንተናዊ ሰላም መረጋገጥ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት የተፈጠሩ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ችግሮችን ለማስተካከልም የመልሶ ማቋቋም ተግባር ውስጥ መገባቱን አንስተዋል።

በጦርነት የተጎዱ መሰረተ-ልማቶችን እና ተቋማትን መልሶ የመገንባትና የልማት ስራዎችን ማፋጠን ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

በዚህም ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ ሰላማዊ ህይወት እንዲመሩ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

መንግስት ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና በመልሶ ግንባታ እያከናወነ ያለውን ተግባር ምሁራን በእውቀታቸው፣ ባለሀብቱ በገንዘቡና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚችለው ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርግ ሚኒስትር ዲኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል የፀጥታ ኃይሉ ከማንኛውም ጸረ-ሰላም ኃይል የሚቃጣን ትንኮሳ በብቃት በመመከት የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ የሚችልበት ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል።

የመከላከያ ሰራዊቱን በአቅም፣ በሞራልና በቴክኖሎጂ በብቃት የመገንባት ስራም በስኬት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጀነራል አዳምነህ መንግስቴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም በማስከበር ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆኗን ገልጸዋል።

በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ለአካባቢው አገራት ጭምር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው፤ ስምምነቱን በሙሉ አቅም በመተግበር ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት መንግስት፣ ህዝብና ባለድርሻ አካላት ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

የሰላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ኮማንዳንት ብርጋዴር ጄነራል ሰብስቤ ዱባ ኢንስትቲዩቱ ከትምህርትና ስልጠና ጎን ለጎን የሰላምና ግጭት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይቶችን እንደሚያዘጋጅ ተናግረዋል።

በዛሬው እለት የተካሔደው መድረክም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሲምፖዚየሙ ጄነራል መኮንኖች፣ ምሁራንና ሌሎች በሰላም ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

በውይይቱ ላይ በድህረ-ግጭት መልሶ ማቋቋምና ሰላም ግንባታ የሲቪል ማህበራት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ሚና ላይ ያተኮሩ የመወያያ ፅሑፎች በምሁራን ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም