የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጸደቀ

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2015(ኢዜአ):- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ።
ምክር ቤቱ በዛሬው 12ኛ መደበኛ ስብሰባው በተጨማሪ በኢፌዴሪ መንግስትና በዓለም አቀፉ የልማት ማህበር መካከል የተደረገውን የብድር ስምምነት እንዲሁም ስለ ራስ--ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል።
ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው በቀዳሚነት ተወያይቶ በአብላጫ ድምጽ ያጸደቀው የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅን ነው።
የረቂቅ አዋጁን የውሳኔ ሃሳብ ያቀረቡት በምክር ቤቱ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ፤ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ሁሉን አቀፍ፣ ወጥና አስተማማኝ በሆነ መልኩ የአገሪቱ ነዋሪዎች የሚመዘገቡበትን ስርዓት ይዘረጋል ብለዋል።
መታወቂያውን በመጠቀም በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ የግልጽነትና ተጠያቂነት ስርዓት እንዲዘረጋና የተሳለጠ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት እንዲኖር አመቺ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ሲሉም አክለዋል።
አዋጁ ረዘም ላለ ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ያሉት ሰብሳቢዋ ግለሰቦችና ተቋማት የተጭበረበረ መታወቂያ ሰጥተው ከተገኙ ከበድ ያለ ቅጣት እንደሚጥልም ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ በጉዳዩ ዙሪያ ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1284/2015 አድርጎ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።
ምክር ቤቱ በመቀጠል ተወያይቶ ያጸደቀው በኢፌዴሪ መንግስትና በዓለም አቀፉ የልማት ማህበር መካከል የተደረገውን የብድር ስምምነት ነው።
የስምምነቱን የውሳኔ ሃሳብ እና ሪፖርቱን የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ አቅርበዋል።
በዚህም የብድር ስምምነቱ ዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮጀክትን በማስፈጸምና የመሬት ልማት ስራዎችን ለመስራት፣ ዘመናዊ የመሬት አያያዝን ለማስፈን ወሳኝ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የተራቆቱ መሬቶችን ለማልማት፣ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ስራዎችን ለማጠናከር እንዲሁም የመሬት ምርትና ምርታማነት እድገትን በማጠናከር የአርሶ አደሩን ገቢ እና አኗኗር እንደሚያሻሽል አመልክተዋል።
ምክር ቤቱም የውሳኔ ሃሳብ ሪፖርቱን ካዳመጠ በኋላ የብድር ስምምነቱን በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ ስለ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይም ውይይት አድርጓል።
በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ የሰጡት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ናቸው።
በማብራሪያቸውም ዩኒቨርሲቲዎቹ ራስ-ገዝ እንዲሆኑ መታሰቡ ለተቋማት ውጤታማነት፣ አካዳሚያዊና ተቋማዊ ነጻነት እንዲኖራቸው፣ የራሳቸውን የገቢ ምንጭ እንዲያስፋፉ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ብለዋል።
ምክር ቤቱ በአዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየበት በኋላ ረቂቅ አዋጁ አዋጅ ቁጥር 16/2015 ሆኖ ለዝርዝር እይታ ለሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ለህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቶታል።