ቀጥታ፡

የሽግግር ፍትሕ ጉልህ ለሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነትን በማስፈን እርቅና ይቅርታን መፍጠር መሰረት ያደረገ ነው-ዶክተር ማርሸት ታደሰ

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2015(ኢዜአ)፦ የሽግግር ፍትሕ ለተፈጸሙ ጉልህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነት በማስፈን እርቅና ይቅርታን መፍጠር መሰረት ያደረገ መሆኑን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ጥናት ባለሙያ ዶክተር ማርሸት ታደሰ ገለጹ።

የሽግግር ፍትሕ ጽንሰ ሃሳብን ለማጎልበት ያለመ የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ የአውደ ጥናት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
 
የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ አዘጋጅ የባለሙያ አባላት፣ የሕግና የሰብአዊ መብት ጥበቃ ባለሙያዎችን ጨምሮ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
 
የመድረኩ ዋና ዓላማ የሽግግር ፍትህ ጽንሰ ሃሳብ ግልጸኝነትን በመፍጠር የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማሳደግ  መሆኑ ተገልጿል።
 
የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ጥናት የባለሙያዎች አባል ዶክተር ማርሸት ታደሰ፤ ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ ጉልህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችንና ቁርሾዎችን ለመፍታት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
አገራት ከግጭት ወደ ሰላም በሚያደርጉት የሽግግር ሂደት ፍትህ፣ እውነትና እርቅን ለማስፈን እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
  
በሽግግር ፍትሕ ሂደት ላይ ጉልህ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትን ለይቶ ተጠያቂ በማድረግ ተጎጂዎች ፍትሕ  እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል። 
 
በሂደቱም እውነትን ማፈላለግ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ነው ዶክተር ማርሸት የተናገሩት።
 
የሽግግር ፍትሕ በመደበኛ የፍትሕ ስርዓት ሊዳኙ የማይችሉ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ የሚተገበር የፍትሕ ሂደት መሆኑንም ገልጸዋል።
 
የምክክር መድረኩን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ምክር ቤትና የደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት በጋራ በመሆን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም