ቀጥታ፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ የዜጎች ሕልም እንዲሳካ የህዝቡ ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት--የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት አወሉ አብዲ

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2015 (ኢዜአ):-የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ የዜጎች ምኞት እውን እንዲሆን ሁሉም ወገን የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት አወሉ አብዲ ገለጹ።

የሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት 12ኛ ዓመት በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በአርሲ ዞን በፎቶ አውደ ርዕይና በፓናል ውይይት እየተከበረ ነው።

የክልሉ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ አወሉ አብዲ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ለማብቃት ሕዝቡና የለውጡ አመራር የማይተካ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።


 

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን በመቋቋም የግድቡ ግንባታ ለአፍታም ሳይቋረጥ በተጠናከረ መልኩ ማስቀጠል መቻሉን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ የአባይ ወንዝ ለዘመናት ሳይለማ የባዕድ ሀገር ሲሳይ ሆኖ መቆየቱ ባሳደረበት ቁጭት የግድቡ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ ርብርብ እያደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም በ2014 ዓ.ም የሕዳሴ ግድብ ዋንጫ በክልሉ በነበረው ቆይታ ከ1 ቢሊዮን 48 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ ዳግም ለግድቡ ግንባታ ዳር መድረስ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ።

ሕዝቡ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ ዘንድሮም በተፋሰስ ልማትና በቦንድ ግዢ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉንም አመልክተዋል።


 

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዶክተር አረጋዊ በርሔ በበኩላቸው ሕዝቡ በግድቡ ላይ በውጭ ሚዲያዎች የሚደረገውን ዘመቻና በአገር ውስጥ የነበሩ ችግሮች ሳይበግሩት ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ፈተናዎች ውስጥ በነበረችበት ወቅት የኦሮሚያ ክልል ያደረገው ድጋፍ ዳግም ኢትዮጵያዊ ጀግንነቱን ያረጋገጠ ነው” ብለዋል።

አሁንም ቀሪ የግንባታ ሂደት እስኪጠናቀቅ ሕዝቡ የጀመረውን ሁሉን አቀፍ ርብርብ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሮሚያ ክልል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ቆንጂት በቀለ የክልሉ ሕዝብ በ12 ዓመታት ውስጥ ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

12ኛ ዓመቱን በማስመልከት የተዘጋጀው የቦንድ ሽያጭ በክልሉ እየተከናወነ እንደሚገኝና እስከ አሁን ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዥና በስጦታ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 12ኛ ዓመት በዓል ላይ ባለሃብቶችን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም