የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትየጵያ ዜና አገልግሎት መተዳደሪያ ደንብን ለማዘጋጀት የቀረበ መነሻ ሃሳብን ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2015 (ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መተዳደሪያ ደንብን ለማዘጋጀት የቀረበ መነሻ ሀሳብን ለዝርዝር እይታ ለሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

ምክር ቤቱ 12ኛ መደበኛ ስብስባውን ዛሬ አድርጓል።

መነሻ ሃሳቡን ያቀረቡት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በተለያዩ ወቅቶች ከአደረጃጀት ጋር በተያያዘ የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት እንደነበር አውስተው፤ አገልግሎቱ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠርና አገራዊ ገጽታን የመገንባት ተልዕኮ የተሰጠው ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።


 

ይሁን እንጂ በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ያለውን የተለያየ ጫና ተቋቁም በአዋጅ የተሰጠውን ተልዕኮ እንዲወጣ በየጊዜው ሲደረግ ከነበረው ጥገናዊ ለውጥ ወጥቶ ተወዳዳሪና ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አመልክተዋል።

ምክር ቤቱም ማብራሪያውን ካዳመጠ በኋላ ረቂቅ ደንብ ቁጥር 02/2015 አድርጎ ለዝርዝር ዕይታ ለሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም