ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት በሙሉ መተማመን እየደገፈ ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

256

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2015(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት በሙሉ መተማመን እየደገፈ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ገለፁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ላይ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ከሳዑዲ ዜጎችን የማምጣት ተግባር ከተጀመረ አንድ ዓመት የሞላው ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ 125ሺህ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ቤት መመለስ መቻሉንም ተናግረዋል።

ሳምንቱ በሰላም፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካዊ ዲፕሎማሲ ጠንካራ እንቅስቃሴ የተደረገበት ነው ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት በሙሉ መተማመን እየደገፈ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት በዘላቂነት ለማቆም በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት በመፈጸም ረገድ መንግሥት በርካታ ስራዎችን ማከናወኑንም ነው ያነሱት።

መሰረታዊ አገልግሎችን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉ እንዲሁም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መመስረቱ የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም እንዲሁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የሰላምና ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን አስተሳስሮ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በማስፈን በጋራ ለመልማት ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ትሰራለች ብለዋል።

በተለይም ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም