በለውጡ ሂደት በሁሉም መስክ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችሉ ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል-የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ

269

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2015(ኢዜአ)፦ ባለፉት አምስት የለውጥ ዓመታት ያጋጠሙ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመለወጥ ለዜጎች የምትመችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ "ኢትዮጵያ በቅድመ 2010ዓ.ም በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በርካታ ፈተናዎች ገጥመዋት በቁልቁለት ጉዞ ላይ እንደነበረች" አስታውሰዋል።

በተለይም የሥራ አጥነት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የፕሮጀክቶች መጓተትን ጨምሮ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በከፍተኛ ደረጃ የሚጣሱበት ሁኔታ እንደነበር ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት የታፈነበትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ጭላንጭል ጠፍቶ የነበረበት አጋጣሚ እንደነበርም ምክትል ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።

የዜግነት ዲፕሎማሲ የተገፋበት፣ የሀገር ጥቅም ቅድሚያ የማይሰጥበት፣ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተዛባ ግንኙነት የነበረበት አገርና ህዝብን የሚጎዳ አካሄድ እንደነበርም ገልጸዋል።

በእነዚህ እና በሌሎችም ተደራራቢ ችግሮች ኢትዮጵያ በቁልቁለት ጉዞ ላይ ትገኝ ነበር ብለዋል አቶ አደም።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ግን ባለፉት አምስት አመታት በርካታ ውስብስብ አገራዊ ችግሮችን በመፍታት ለዜጎች የምትመችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

በሂደቱ በርካታ ፈተናዎችና ውጣ ውረዶች ቢያጋጥሙም ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመለወጥ በተለያዩ መስኮች ተጨባጭ ውጤቶች መምጣታቸውን አብራርተዋል።

በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውና በዲፕሎማሲው መስክ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ አካታችና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሥርዓት በመከተል የተሳካ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።

የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትም የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች ተደርገው ሁሉንም አሳታፊ የሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ማኖር ተችሏል ነው ያሉት።

ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመለወጥ ስልትም በኢኮኖሚው መስክ የዕዳ ጫናን በማቃለልና ምርታማነትን በማሳደግ የላቀ አፈፃፀም መመዝገቡን አንስተው፤ በተለይም በስንዴ ልማት፣ በቡና፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ የተገኙትን ውጤቶች ለአብነት ጠቅሰዋል።

የቱሪዝም አቅምን የመጠቀም፣ በሌማት ቱርፋት፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ የተመዘገበው ስኬትም ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

በፖለቲካው መስክ የሀሳብ ብዝሃነት እንዲከበር፣ ስልጣን በሀሳብ ልዕልና እንዲያዝ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረው በ6ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ የታየውን ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደትም አንስተዋል።

በዲፕሎማሲው መስክ ጎረቤት ሀገራትን ያስቀደመ የትብብር ግንኙነትና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በመከተል የኢትዮጵያን ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅም፣ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

በቀጣይም የተጀመሩ ስኬታማ ሥራዎችን በማስቀጠል ፈተናዎችን ተጋፍጦ በማሸነፍ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መንግስት በቁርጠኝነት የሚሠራ መሆኑን አቶ አደም አረጋግጠዋል።

የተቋማት ግንባታና የዴሞክራሲ ባህልን ማጠናከር፣ ምርታማነትን መጨመር፣ ሌብነትና ጽንፈኝነትን መታገል፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ በቀጣይም ቁልፍ ሥራዎች ሆነው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት መፍጠር፣ አገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን መሥራትና የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሥራ ላይ ውሎ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ በማድረግ ሂደት የመንግስት ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም