ስምንት የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጣና ስራ ለመጀመር የሚያስችል ስምምነት ፈጽመዋል - ኢዜአ አማርኛ
ስምንት የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጣና ስራ ለመጀመር የሚያስችል ስምምነት ፈጽመዋል
አዲስ አበባ መጋቢት 21/2015 (ኢዜአ) ስምንት የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና በመግባት ማልማት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈጸማቸውን የድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጣና አስታውቋል፡፡
የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና የጎረቤት ሀገራትን የንግድ እሴት ሰንሰለት ከማጠናከር ባለፈ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ የንግድ ትስስርን እየተቀላቀለች መሆኑን ያሳያል ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ ተናግረዋል።
በመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አዘጋጅነት የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና እና በድሬዳዋ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የመስክ ጉብኝት አድርገዋል።
የድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጣና ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ረሺድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ቀደም ሲል በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የነበሩ አምራች ድርጅቶች በነጻ ንግድ ቀጣናው ታቅፈው ስራቸውን ቀጥለዋል።
ተጨማሪ ስምንት ድርጅቶች ስምምነት ፈጽመው ወደ ነጻ ንግድ ቀጣናው ለመግባት በለማ መሬት ላይ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በድሬዳዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈተው ነጻ የንግድ ቀጣና ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ከቀረጥ ነጻ የሚስተናገዱበት፣ ያለምንም እንግልት ከወደብ በቀጥታ ተሻግሮ የሚገበያይበት ስፍራ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ነጻ የንግድ ቀጣናውን ከድሬዳዋ የባቡር ሃዲድ ጋር በማገናኘት ጭነቶችን በቀላሉ ማስተናገድ የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የድሬዳዋ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ እመቤት ፍስሐ በበኩላቸው በ2005 ዓ.ም የተጀመረው የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቆ በዓመቱ መጀመሪያ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።
ደረቅ ወደቡ በዩኒሞዳል እና መልቲ ሞዳል የሎጀስቲክስ አገልግሎት በመስጠት የሀገሪቱን የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ በማሳለጥ የበኩሉን ጉልህ ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
በደረቅ ወደቡ ሁሉም ደንበኞች የሚገለገሉበት የአንድ መስኮት አገልግሎት መከፈቱንም አስታውቀዋል፡፡
ደረቅ ወደቡ የንግድ እንቅስቃሴውን ከማዘመን ባሻገር ለአካባቢው ወጣቶች የስራ ዕድል በመክፈት የማይናቅ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ እንደገለጹት የድሬዳዋ የነፃ ንግድ ቀጣና ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
ነፃ የንግድ ቀጣናው የበይነ አፍሪካ የንግድ ትስስር ስርዓትን ለማዘመን ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
ለጅቡቲ ወደብ ካለው ቅርበት አንፃር የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና መከፈቱ የአምራች ዘርፉን ማነቆ ለመቅረፍ እንደሚያስችልም ገልፀዋል።
ከአምስት ዓመታት ወዲህ 40 የአፍሪካ ሀገራት ነፃ የኢኮኖሚ ዞን መገንባታቸውን ጠቅሰው፤ ይህም የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራን ለማሳለጥ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጠር ገልፀዋል።
ቀጣናው የጎረቤት ሀገራትን የንግድ እሴት ትስስር ለማጠናከርና ፓን አፍሪካኒዝምን ከፖለቲካ ወደ ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ሁነኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
በማዕከሉ ስራ የጀመሩ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ኩባንያዎችና ሌሎች አምራቾች የንግድ ቀጣናው በተለይም ለጅቡቲ ቅርብ መሆኑ የሎጀስቲክ ችግርን የሚቀርፍ ነው ብለዋል።
መገናኛ ብዙኃን ስለነፃ ንግድ ቀጣናው መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ መስራት አለባቸው ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል።