በአዲስ አበባ ከተማ የ “መደመር ትውልድ” የወጣቶችና ሕጻናት የመጫወቻና ስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐግብር እየተካሄደ ነው

494

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2015(ኢዜአ)፦ ከ “መደመር ትውልድ” መጽሐፍ ሽያጭ ከሚገኝ ገቢ ለሚገነቡ የሕጻናትና ወጣቶች የመጫዎቻና የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐግብር በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።

በመርሐግብሩ አማካኝነት በ11ዱም ክፍለ ከተሞች በተመሳሳይ አንድ የስፖርት ማዘውተሪያና የመጫወቻ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ መርሐግብር ተከናውኗል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በነፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ቆሼ አካባቢ ቴኒስ ሜዳ፣ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ፈረንሳይ እየሱስ ሜዳና በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት የስፖርት ማዘውተሪያና የመጫወቻ ማዕከላት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

ከ “መደመር ትውልድ” መጽሐፍ የሚገኘው ገቢ ለወጣቶችና ሕጻናት የመዝናኛ ስፍራዎችን ለመገንባት እንዲውል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በስጦታ ማበርከታቸውን ከንቲባ አዳነች አስታውሰዋል፡፡


 

“የመጽሐፉ ሽያጭ የሚካሄደው ገቢ ማግኛ ብቻ ሳይሆን ትውልድ የሚገነባበት ታላላቅ ሃሳቦች በውስጡ የያዘ ነው” ብለዋል።

ያለፋት ትውልዶች የሰሩት መልካም ተግባርና ጉድለቶች አሉ ያሉት ከንቲባዋ ከእነሱ የተሻለውን በመማር አገር የሚገነባ ትውልድ ለመፍጠር ሃሳብና ምቹ ስፍራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የሚገነቡት የወጣቶችና ሕጻናት የመጫወቻና ስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት በሶስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱ ተገልጿል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች፣ ነዋሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም