ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በደብረብርሀን ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ

  ደብረ ብርሃን መጋቢት 20/2015 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በደብረ ብርሀን ከተማ  በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር   ግምት ያለው  የምግብ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ የተደረገው ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ  በተለምዶው ወይንሸት ካምፕ ተብሎ በሚጠራ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች ነው።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሰሜን ሸዋ ዞን ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ዳምጠው እምሻው  ዛሬ በተካሄደ የድጋፍ ርክክቡ ስነ ስርአት ላይ እንዳሉት ማህበሩ በተለያየ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

ድጋፉ 400 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ ሩዝ፣ ፓስታ፣ ማኮረኒ ጨምሮ  1ሺህ 200 ሊትር የምግብ ዘይት ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሀላፊው አስታውቀዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግዛቸው ለገሰ በበኩላቸው በደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር 30 ሺህ የሚደርሱ ተፈናቃይ ወገኖች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ከተፈናቃይ ወገኖች ቁጥር አንፃር የጤና፣ የእለት ደራሽ ምግብና የመጠለያ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤  "በቀይ መስቀል ማህበር በኩል እየተደረገ ያለው ድጋፍ  ችግሩን ለመቀነስ እያገዘ ነው" ብለዋል።

በወቅታዊ ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች ከመንግስትና ሌሎች አካላት እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ።

ተፈናቃይ ወገኖችም  ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

 

 

 

 

    

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም