የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ አዋጁ በተጨማሪ ውይይቶች መዳበር አለበት - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ አዋጁ በተጨማሪ ውይይቶች መዳበር አለበት - ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ/መጋቢት 20/2015 (ኢዜአ)የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ አዋጁ በተጨማሪ ውይይቶች እንዲዳብር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅጣጫ ሰጠ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብ ይፋዊ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የኤክሳይዝ ታክስ ዓላማ ለመንግሥት ተጨማሪ ገቢ ማስገኘትና በኅብረተሰቡ ላይ የጤና ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶች ፍጆታን መቀነስ መሆኑ ተገልጿል።
እንዲሁም ከፍተኛ ሃብት ያላቸው ሰዎች ከሚጠቀሙባቸው የቅንጦት እቃዎች ላይ ገቢ በመሰብሰብ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ህይወት ማሻሻል መሆኑ ተገልጿል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት ዓላማ ከዚህ ቀደም በነበረው አዋጅ ማሳካት ያልተቻሉ ግቦችን ለማሳካት ነው።
የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ በመከተል የታክስ ሕጎች በየጊዜው ማሻሻያ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የውኃ ፋብሪካዎች በታሸገ ውኃ ላይ የተጣለው የኤክሳይዝ ታክስ አግባብ አለመሆኑንና ውኃ እንደ ቅንጦት ዕቃ ሊወሰድ አይገባም ነው ያሉት።
በአልኮልና ትምባሆ ምርቶች ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችም የተጣለው የኤክሳይዝ ታክስ የተጋነነና ተጠቃሚዎች ወደ ሌላ ጥራቱን ወዳልጠበቀ ምርት እንዲሄዱ ያደርጋል ብለዋል።
እንዲሁም ለሕገ-ወጥ ምርቶች በስፋት መበራከት በር ከፋች መሆኑንና በእነዚህ ፋብሪካዎች የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውን ዜጎች የሚጎዳ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ማኅበራት ተወካዮች በበኩላቸው፤ የኅብረተሰቡን ጤና በሚጎዱ ምርቶች ላይ የተጣለው ታክስ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
በእነዚህ ፋብሪካዎች ከሚሰሩ ዜጎች ይልቅ ቁጥራቸው ከእጥፍ በላይ የሆነ አምራች ዜጎች በእነዚህ ምርቶች ህይወታቸውን እንደሚያጡ ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በዋናነት የዚህ ኤክሳይዝ ታክስ ዓላማ ለጤና ጎጂ የሆኑ ምርቶችን ዝቅ ማድረግ ነው።
በማሻሻያ አዋጁም ይህ ዓላማ ተጠናክሮ የሚቀጥልና የሚቀንስ ነገር አለመኖሩን ገልጸዋል።
በአልኮል ላይ የተጣለው የኤክሳይዝ ታክስ የተሻሻለው ተደራራቢ ታክስ እንዳይፈጠር መሆኑንና ግብዓቱ ላይ ብቻ የተደረገ ማሻሻያ መሆኑን ጠቁመዋል።
ውኃን በተመለከተ በሰጡት ምላሽም ከታሸገ ውኃ በሚገኘው ታክስ ሌሎች ውኃ ማግኘት ያልቻሉ ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ልማት የሚከናወንበት መሆኑን አስረድተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ፤ አዋጆች ሥራ ላይ ሲውሉ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የተሰጡ አስተያየትና ግብዓቶች ጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ሰብሳቢው፤ በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶች እንደሚዳብር ተናግረዋል።
የሚጣለው ኤክሳይዝ ታክስ ተገቢና በመርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ታምኖበት ሥራ ላይ እንዲውል ቋሚ ኮሚቴው ጥረት እንደሚያደርግም ነው የገለጹት።
በአሁኑ ጊዜ ሥራ ላይ ያለው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 1186/2012 ከየካቲት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ላይ መዋሉ ይታወሳል።
የኤክሳይዝ ታክስ ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች ተብለው ከሚታወቁት በዕቃና በአገልግሎት ላይ ከሚጣሉ ታክሶች ምድብ ውስጥ የሚገኝ የታክስ ዓይነት ነው።