በሶስተኛው የኢትዮጵያ ፓራኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና መክፈቻ አራት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል

349

አዲስ አበባ መጋቢት 20/2015(ኢዜአ)፦ በሶስተኛው የኢትዮጵያ ፓራኦሊምፒክ አትሌቲክስ ሻምፒዮና መክፈቻ ቀን አራት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል።

የኢትዮጵያ ፓራኦሊምፒክ ኮሚቴ ያዘጋጀው ሻምፒዮና በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዛሬ ተጀምሯል። 

በውድድሩ ላይ ከአምስት ክልሎችና ሁለት ከተማ መስተዳደሮች የተወጣጡ ወንድ 254 ሴት 126 በድምሩ 380 ስፖርተኞች ተሳታፊ ናቸው።

በተጨማሪ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚና የኦሮሚያ ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ክለብ በውድድሩ ተሳታፊ መሆናቸው ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ፓራኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ጊዮን ሰይፋ (ዶ/ር) ውድድሩ ተቀዛቅዞ የቆየውን የፓራኦሊምፒክ ስፖርት ማነቃቃትና በቀጣይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፋ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ታስቦ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በውድድሩ መክፈቻ አራት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል።

በሴቶች 100 ሜትር የእጅ ጉዳት በሴቶች 100 ሜትር የእጅ ጉዳት የፍፃሜ ውድድር አትሌት ሀያት ይማም ከአማራ ክልል አሸንፋለች።

አትሌት ዝናሽ አሳይ ከኦሮሚያ ክልል ሁለተኛ እንዲሁም አትሌት ሉባባ ዘውዴ ከአማራ ክልል ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። 

በወንዶች 100 ሜትር አይነስውራን ጭላንጭል አትሌት ኤርሚያስ ቱሉ ከኦሮሚያ ክልል አሸናፊ ሆኗል።

አትሌት ይሄነው ካሳሁን ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሁለተኛ ሲወጣ አትሌት ልዑል መረሳ ከአዲስ አበባ  ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

በሴቶች አሎሎ ውርወራ የእግር ጉዳት አትሌት ሀዳስ ምሩፅ ከአዲስ አበባ አንደኛ ወጥታለች።

አትሌት ሚሚ ሚካኤል ከሲዳማ ክልልና አትሌት አዳነች ፍቃዱ ከኦሮሚያ ክልል በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በወንዶች 800 ሜትር የዊልቸር አትሌት ደምስ አበራ ፣ አትሌት ምህረት ባዜና አትሌት ፀሐይነህ ተፈራ ሁሉም ከአዲስ አበባ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ በላይነት አጠናቀዋል።

ከፍጻሜ ውድድሮች በተጨማሪ በተለያዩ ርቀቶች የማጣሪያ ውድድሮች ተከናውነዋል።

ሶስተኛው የኢትዮጵያ ፓራኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ መጋቢት 24 2015 እንደሚቆይ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም