ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ከዓለም ፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ፕሬዝዳንት ዊቶልድ ባንካ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ መጋቢት 20/2015(ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ከዓለም ፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ(ዋዳ) ፕሬዝዳንት ዊቶልድ ባንካ ጋር ኢትዮጵያና ኤጀንሲው ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልባችው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

ዋዳ ለኢትዮጵያ የሚያደርጋቸውን ድጋፎች የተመለከተ ምክክር መደረጉንም ከፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


 

ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላትና አትሌት አበበ ቢቂላ በሮም ማራቶን ድል ካደረገ ጊዜ ጀምሮ በዓለም መድረክ እውቅናዋ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ዋዳ በፀረ- አበረታች ቅመሞች ቁጥጥር ዙሪያ ለሚያደርጋቸው የቴክኒክ ድጋፎች ምስጋና አቅርበዋል።

የዓለም ፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ፕሬዝዳንት ዊቶልድ ባንካ ከቀናት በፊት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መወያየታቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም