ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የአጭር ርቀት የአትሌቲክስ ስፖርት ትኩረት በማጣቱ አትሌቶች ወደ መካከለኛና የረጃጅም ርቀት ውድድር ለመዞር እየተገደዱ ነው- አሰልጣኞች

አዲስ አበባ መጋቢት 20/2015 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የአጭር ርቀት የአትሌቲክስ ስፖርት ትኩረት በማጣቱ አትሌቶች ወደ መካከለኛና የረጃጅም ርቀት ውድድር ለመዞር እየተገደዱ መሆኑን በዘርፉ የተለያዩ አሰልጣኞች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ኢትዮጵያ በአጭር ርቀት ውጤታማ እንድትሆን በቀጣይ ብዙ መሥራትን ይጠይቃል ብሏል።

ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት አትሌቲክስ ስፖርት ስማቸው ከፍ ብሎ ከሚነሱ የዓለም ሀገራት መካከል በቀዳሚነት ትጠቀሳለች።

በረጅም ርቀት ከፍ ያለ ስምና ታሪክ ቢኖራትም በተለይም በአጫጭር ርቀቶችና የሜዳ ላይ አትሌቲክስ ስፖርት ያላት ተሳትፎና ፉክክር ደካማ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በዚሁ ዙሪያ ኢዜአ ካነጋገራቸው የአትሌቲክስ አሰልጣኞች መካከል ዋና ኢንስፔክተር አሰልጣኝ አብዱልሸኩር ተማም፤ የአጭር ርቀት የአትሌቲክስ ውድድር እምብዛም ትኩረት የተሰጠው አለመሆኑን ይናገራሉ።

አብዛኞቹ ውድድሮች የሚደረጉት በሀገር ውስጥ ብቻ የተወሰኑ በመሆኑ በርቀቱ አትሌቶችን ለማፍራት አዳጋች አድርጎታል ብለዋል።

በዚህም ምክንያት በርካታ አትሌቶች ከአጭር ርቀት ወደ መካከለኛና የረጃጅም ርቀት ውድድሮች ለመግባት መገደዳቸውን አሰልጣኙ ገልጸዋል።

ሌላኛው አሰልጣኝ ጌታቸው ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአጭር ርቀት ሰፊ ውድድር ካላቸው የስፖርት ዓይነቶች አንዱ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን ትኩረት የተነፈገው ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ለአጭር ርቀት ስፖርት አስፈላጊ ከሚባሉት ነገሮች መካከል የመለማመጃ ትራክና የሥልጠና ቁሳቁስ እጥረት መኖሩንም ጠቅሰዋል።

እንደ ሀገር ትኩረት የሚደረገው ለረጅም ርቀት በመሆኑ በአጭር ርቀት ውጤታማ መሆን አለመቻሉን የሚናገሩት ደግሞ አሰልጣኝ ወጠሬ ገለልቻ ናቸው።

በመሆኑም ዘርፉ ትኩረት ቢሰጠው በአህጉርም ይሁን በዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያን የሚወክሉ በርካታ አትሌቶችን ማፍራት እንደሚቻል ይናገራሉ።


 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበኩሉ፤ ኢትዮጵያ በአጭር  ርቀት ውጤታማ እንድትሆን በቀጣይ በርካታ ሥራዎችን ይጠይቃል ብለዋል።

በፌዴሬሽኑ የትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክተር ሳሙኤል ብርሃኑ፤ ለዘርፉ ሥልጠና ቴክኒካዊ የሆኑ የተለያዩ ክህሎቶችን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመው፤ የአትሌቶችም ምርጫ በሳይንሳዊ ምዘና ታግዞ ይሰራል ብለዋል።


 

በዚህ ረገድ ፌዴሬሽኑ አጫጭር ርቀት ብቻ ሳይሆን በሜዳ ላይ ተግባርና የረጅም ርቀትም ጭምር የበለጠ ለመሥራት ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።

ለስፖርቱ እድገት ከህፃንነት ጀምሮ መሥራት ስለሚገባ አሁን ላይ በሙከራ ደረጃ የህፃናት የአትሌቲክስ ስፖርት ሥልጠና መጀመሩን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም