ከተለያዩ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች የድሬደዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
ከተለያዩ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች የድሬደዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን ጎበኙ
አዲስ አበባ መጋቢት 20/2015 (ኢዜአ)፦ ከተለያዩ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች የድሬደዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን ጎበኙ።
በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በተሰናዳው የጉብኝት መርሃ-ግብር አጠቃላይ የነፃ ንግድ ቀጣናውን ሂደትና እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም መርቀው የከፈቱት የድሬደዋ ነፃ የንግድ ቀጣና በንግድ፣ በሎጂስቲክስ አገልግሎት እንዲሁም የአምራች ዘርፉ የወጪ ምርቶች ማቀነባበሪያና ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል መሆኑ ይታወቃል።
ለንግድ እንቅስቃሴ መሳለጥ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የዕውቀት ሽግግር እንዲሁም ለአገር ውስጥ ምርቶች የሎጂስቲክስ ወጪን ከመቀነስ አኳያ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ይታወቃል።
የድሬደዋ ነፃ የንግድ ቀጣና በአፍሪካ ደረጃ ወደ ትግበራ ለመግባት በሂደት ላይ ለሚገኘው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት በማሳለጥ ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረውም ይታመናል።
የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ነፃ የንግድ ቀጣና ፕሮጀክት የሆነው የድሬደዋ ነፃ ንግድ ቀጣና ጠቅላላ ስፋቱ 4 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን የድሬደዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና ደረቅ ወደብን ያካተተ ነው።
ማዕከሉ የኢንዱስትሪ ምርት ጥሬ ዕቃዎች የሚከማቹበት፣ የሚቀነባበሩበት፣ የሚገጣጠሙበት እና ወደ ውጭ የሚላኩበት ሲሆን ከድሬደዋ ደረቅ ወደብ ጋር ተሳስሮ ገቢራዊ የሚደረግ ነው።
የድሬደዋ ከተማ በኢንዱስትሪ መንደርነቷ፣ የደረቅ ወደብ፣ የባቡር፣ የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት መሰረተ-ልማቶች ባለቤት መሆኗ ለነፃ ንግድ ቀጣና ማዕከልነት ተመራጭ አድርጓታል።