ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ዜጎችን የትምህርት እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የጋራ ርብርብ ይጠይቃል

246

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2015  (ኢዜአ) ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ዜጎችን የትምህርት እድል ተጠቃሚ በማድረግ ይበልጥ አምራች ዜጋ እንዲሆኑ  ሁሉም  አካላት በትብብር እንዲሰሩ  በጉዳዩ ላይ የሚሰሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጠየቁ። 

ኒያ ፋውንዴሽን፣ ነህሚያ ኦቲዝም ማዕከል፣ ብራይት ኦቲዝም ማዕከል ሃዋሳ፣ ቤቴል አዳማ ኦቲዝም ማዕከልና ምሉዕ ፋውንዴሽን በጋራ በመሆን  በኢትዮጵያ በኦቲዝም የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአሳሳቢ ደረጃ እየጨመረ መሆኑን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።   

በኒያ ፋውንዴሽን የጆይ ኦቲዝም ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ እሌኒ ዳምጠው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የኦቲዝም እክል ብዙም ትኩረት ባለመሰጠቱ በቤተሰቦቻቸውና በማኅበረሰቡ ብዙ እንግልት እየደረሰባቸው ይገኛሉ። 

በተለይ ደግሞ የአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩ ዜጎች በቂ የሆነ እድል የሚሰጥ አይደለም ብለዋል። 

በዚህም ምክንያት ከራሳቸው አልፈው ለአገርና ቤተሰብ አለኝታ መሆን የሚችሉ በርካታ ዜጎች ባክነው ይቀራሉ ነው ያሉት። 

ይህን ችግር መነሻ በማድረግ ጆይ ኦቲዝም ማዕከል አስራ ሁለት ልጆችን አስተምሮ በማብቃት በግቢው ውስጥ ሥራ እንዲይዙ አደርጓል ብለዋል።

በዚህም እነዚህ ዜጎች የራሳቸውን ህይወት ከመደጎም ባለፈ ከደሞዛቸው ተቆራጭ እየሆነ ለመንግሥት ግብር ማስገባት መጀመራቸውን ጠቁመዋል። 

በአሁኑ ወቅትም 80 ልጆችን በማቀፍ የማስተማርና የመንከባከብ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አመላክተዋል። 


 

በመሆኑም የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ዜጎችን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንደሚገባው ነው ያመላከቱት።

የነህሚያ ኦቲዝም ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ ራሔል አባይነህ በበኩላቸው እነዚህ ልጆች ድጋፍና ትምህርት ከተሰጣቸው እንደማንኛውም ሰው አምራች ዜጋ መሆን እንደሚችሉ ጠቁመዋል። 

ዜጎቹ በተለይም በትምህርት ሥርዓት ውስጥ የሚካተቱበትን ሁኔታ ለማጠናከር መስራት ይገባል ብለዋል።

ብራይት ኦቲዝም ማዕከል ሃዋሳ ዋና ሥራ አስኪያጅ ትዕግስት አበበ በበኩላቸው ተቋማቸው እነዚህ ዜጎች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት እንዲወጡ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። 

በመሆኑም የትምህርት እድል እንዲሰጣቸው በማድረግ ራሳቸውን እንዲችሉ ሁሉም ሊተባበር ይገባዋል ነው ያሉት።  

የቤቴል አዳማ ኦቲዝም ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ገነት ንጉሴና የምሉዕ ፋውንዴሽን ኦቲዝም ማዕከል  ዋና ሥራ አስኪያጅ ትዕግስት ሃይሉ በበኩላቸው፤ ማዕከላቸው በኦቲዝም የተያዙ ልጆችን በማሰባሰብ የህይወት ክህሎት ሥልጠና እየሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

እነዚህ ዜጎች ራሳቸውን ብቁ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ድጋፎች እንዲያገኙ መሥራት የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል። 

አምስቱ የኦቲዝም ማዕከላት የኦቲዝምን ችግር ያለባቸውን ዜጎች መብት ለማስከበርና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል የኢትዮጵያ ኦቲዝም ሶሳይቲን ለመመሥረት መግባባት ላይ ደርሰዋል። 

በቀጣይም ሌሎች በመስኩ የተሰማሩ ተቋማትን እያካተቱ እንደሚሔዱ ተናግረዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም