የሕዝቦችን ሁለንተናዊ ትስስር ለማጠናከር እንሰራለን - የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳደሮች  

109

ጅግጅጋ መጋቢት 19/2015 (ኢዜአ) ጅግጅጋ መጋቢት 19/2015 (ኢዜአ) ፡- በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ሕዝቦች መካከል የቆየውን ሁለንተናዊ ትስስር በልማት ለማጠናከር እንደሚሰሩ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳደሮች ገለጹ።

ርዕሳነ መስተዳደሮቹ ይህንን የገለጹት፤ የኦሮሚያ ክልል በመደበው 40 ሚሊዮን ብር ውጪ በጅግጅጋ ከተማ የተገነባ "ካህ" ተብሎ የተሰየመውን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ በጋራ ሲመርቁ ነው። 


 

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በጅግጅጋ ከተማ የተገነባው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች በልማት ለማስተሳሰር ከተከናወኑ ስራዎች አንዱ ማሳያ ነው። 

አቶ ሽመልስ "የሁለቱን ሕዝቦች የቆየ ትስስር ለማጠናከርና በልማት ለማስተሳሰር ያስገነባነው ይህ ትምህርት ቤት በቀጣይ አገርን የሚመሩ ወጣት ምሁራን የሚወጡበት ይሆናል" ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ በበኩላቸው፤ "የኦሮሚያ ክልል ያስገነባው ትምህርት ቤት ከወንድም ሕዝብ  የተደረገልን ትልቅ ስጦታ ነው" ብለዋል።

"የሁለቱ ሕዝቦች ያላቸው ሁለንተናዊ ትስስር በልማት ለመደገፍና በጋራ ለማደግ የያዙትን ጥረት ስኬታማ መሆኑን ይህ ትምህርት ቤት በማሳያነት የሚጠቀስ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ  የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች እንዲማሩበት ይሰራል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ትምህርት ቤቱን ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ጋር ለማስተሳሰር መታቀዱንም ጠቁመዋል። 

ባለ ሁለት ወለል ሕንጻ የሆነው ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍል፣ ቤተ-መጻሕፍት ፣ ቤተ-ሙከራና የአስተዳደር ክፍሎችን ያካተተ ነው። 

በስነ ስርዓቱ ላይ  የሁለቱ ክልሎች  ከፍተኛ አመራሮች ፣  የጎሳ መሪዎች፣ የኃይማኖት አባቶች ፣ወላጆችና ተማሪዎች፣ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም