ኢትዮጵያና ጃፓን በሆርቲካልቸር ልማት ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

156

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2015 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያና ጃፓን በሆርቲካልቸር ልማት ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ የአነስተኛ አርሶ አደሮችን የሆርቲካልቸር አቅም ማጎልበቻ ፕሮጀክት ሁለተኛ ምዕራፍ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።

የግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር መለሰ መኮንንና የጃፓን አለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሞሪሃራ ካሱኪ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

አነስተኛ አርሶ አደሮች የሆርቲካልቸር አቅም ማጎልበቻ ፕሮጀክት በምዕራፍ አንድ አማራ እና ኦሮሚያ ክልል ሲተገበር መቆየቱ ተገልጿል።

በስምምነቱ መሰረት የፕሮጀክቱ ሁለተኛ ምዕራፍ በደቡብና ሲዳማ ክልሎች እንደሚተገበር ተጠቁሟል።

ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር መለሰ መኮንን የጃፓን መንግስት ሆርቲካልቸር ልማት ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመስራት ያለውን ፍላጎት አድንቀዋል፡፡

የጃፓን አለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሞሪሃራ ካሱኪ በፕሮጀክቱ በምዕራፍ አንድ የተከናወኑ ስራዎችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

በምዕራፍ ሁለት የፕሮጀክቱ ትግበራ ጃይካ ለአነስተኛ አርሶ ደሮች በሆርቲካልቸር ልማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም