ሀገራዊ የለውጥ ሂደቱን ማጠናከር እንደሚገባ ምሁራን አመለከቱ

ድሬደዋ  መጋቢት 19 /2015(ኢዜአ) ፡- በየደረጃው  ለሚያጋጥሙ  ችግሮች  የተቀናጀ መፍትሔ በመስጠት የተጀመረውን ሀገራዊ የለውጥ ሂደት ማጠናከር እንደሚገባ ምሁራን አመለከቱ። 

ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲና የተለያዩ ኮሌጆች የተወጣጡ ምሁራን በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ከድሬዳዋ አስተዳደር  አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

ምህራኑ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት ፤ መንግስት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከህብረተሰቡ  ጋር መወያየቱ  ለሚያጋጥሙ ችግሮች የጋራ መፍትሄ ለማምጣት ያግዛል ።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ  የውጭና  የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጋንፉሬ በሰጡት አስተያየት ፤ ባለፉት አራት ዓመታት የመጣው ሀገራዊ ለውጥና  ተከትሎም  የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚስተዋሉ የኑሮ ውድነትና የማህበራዊ አገልግሎት ችግሮች ዜጎችን እያማረሩ በመሆናቸው የተቀናጀ መፍትሔ በመስጠት የተጀመረውን የለውጥ  ሂደት ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።

ይህን መሠል ወቅታዊ ውይይት ማስቀጠል  ዜጎች የሚሰማቸውን  ከማሳወቅ ባሻገር ሁሉም የመፍትሔ አካል እንዲሆን ምቹ ሁኔታ  እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

መምህር ያሬድ ጥበቡ በበኩላቸው ፤ በለውጡ የተገኙ  ሁሉን አቀፍ አበረታች ለውጦችና  ውጤቶች ማጠናከር ላይ መረባረብ ይገባል ብለዋል።

ለሚያጋጥሙ  ችግሮች  በተቀናጀ አግባብ  መፍትሄ በመስጠት  የለውጡን ሂደት ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል። 

በተለይ በድሬደዋ የሚስተዋለው የኑሮ ውድነትና የመልካም አስተዳደር  ችግሮችን ለመፍታት መንግስት በአፋጣኝ የመፍትሄ  እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር በነዳጅ ማደያዎች  ውስጥ እየተስፋፋ ለሚገኘው ህገ ወጥና የተበላሸ አሰራር  አፋጣኝ መፍትሔ በመስጠት ከትራንስፖርት አገልግሎት ጋር ለተያያዙ  ችግሮች መፍትሄ መስጠት እንዳለበት የተናገሩት አቶ ወሰን ቢራቱ ናቸው።

 የአከባቢው   ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስቀጠል እንዲሁም ለሚስተዋለው የመልካም አስተዳደር ችግሮች የመፍትሔ አካል በመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል ።

ውይይቱን ከመሩት መካከል የድሬዳዋ አስተዳደር የስራ ክህሎትና የቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው፤ በድሬዳዋ  የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስና  የለወጥ ሂደቱን ለማፅናት ጥናትን መሠረት ያደረገ  የተቀናጀ ሁሉንአቀፍ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን  ገልጸዋል።

እነዚህን ተግባራት ከዳር ለማድረስ  መሰል ውይይቶች በማስፋት ምሁራን ጨምሮ የሌሎችንም የህብረተሰብ ክፍሎችን  ድጋፍና ተሳትፎ እንዲጠናከር  ይሰራል ብለዋል።

በተመሣሣይ  በአስተዳደሩ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች ፣ዑጋዞችና አባገዳዎች እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብና ባለሃብቶች የተሳተፉበት ውይይቶች በሌሎች መድረኮች ተካሂደዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም