ሙስናን ለመከላከል በተቋማት መካከል ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር ይሰራል - የፌደራል ሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
ሙስናን ለመከላከል በተቋማት መካከል ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር ይሰራል - የፌደራል ሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2015 (ኢዜአ) ሙስናን ለመከላከል በተቋማት መካከል ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ የፌደራል ሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ ከ97 የፌደራል ተቋማት ለተውጣጡ ከ270 በላይ የሥራ ኃላፊዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና በቢሸፍቱ እየሰጠ ነው።
ሥልጠናው የሙስና ወንጀል፣ ኦዲትና ሙስናን መከላከል፣ በሥነ-ምግባር ስትራቴጂ ዙሪያዎች ላይ ትኩረት አድርጓል ተብሏል።
የፌደራል ሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ሙስናን ለመከላከል የተቀናጀ አሰራር መዘርጋትና ማጠናከር ወሳኝ ነው።
በተናጠል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውጤት አለማምጣታቸውን ገልጸው ይህንን ክፍተት ለመሙላት የተቀናጀ አሰራር መጠናከር አለበት ብለዋል።
በመሆኑም በተቋማት መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ከተጠናከረ በአገር አቀፍ ደረጃ ሙስናን ለመከላከል የተጀመረው ጥረት ፍሬያማ እንደሚሆን ገልጸዋል።
በአገሪቱ ማኅበራዊ ቀውስን በማስፋፋት ጉልህ ድርሻ የሚጫወተውን ሙስናን ሥነ-ምግባር ችግሮች ሊቀንሱ የሚችሉት በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ጭምር መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ሥልጠና ከተቋማቱ የተውጣጡ የፀረ ሙስናና ሥነ-ምግባር ዳይሬክተሮች፣ የኦዲት ኃላፊዎች፣ የለውጥ አመራሮችና የሕግ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።