በአፍሪካ የኢነርጂ ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የመንግስትና የግሉን ዘርፍ አጋርነት ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ

145

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2015  (ኢዜአ):- በአፍሪካ የኢነርጂ ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የመንግስትና የግሉን ዘርፍ አጋርነት መጠናከር እንዳለበት ተመላከተ።

በአፍሪካ የኃይል ልማትና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ዙሪያ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ በጋራ መስራት በሚችሉት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ጉባኤ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መካሄድ ጀምሯል፡፡    

ጉባኤውን የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ)  እና በአፍሪካ የኃይል ሽግግር ላይ የሚሰራው ሬስ ፎር አፍሪካ ፋውንዴሽን የጣልያን ተቋም በመተባበር ያዘጋጁት ነው። 

አፍሪካ በኢነርጂ ዘርፍ ዕምቅ ሃብት ቢኖራትም በዘርፉ ላይ ያሉ በርካታ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም ተብሏል፡፡  

በአፍሪካ ሕብረት እና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የጣሊያን ቋሚ ተወካይ አልቤርቶ በርቶኒ በአፍሪካ የኢነርጂ ዘርፍን ለማሳደግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለይ በኃይል ማመንጨት፣ በኃይል ስርጭት፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም በከርሰ ምድር ውሃ ቁፋሮ ላይ መንግስትና የግሉ ዘርፍ ተባብረው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።  

የፖሊሲና የቁጥጥር ማዕቀፎች ላይ የሚታዩ ችግሮችን በማሻሻልም ለኢነርጂው ዘርፍ ዕድገት መስራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ይህ ካልሆነ ሕዝቡን ከዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ አዳጋች ነው ብለዋል።

ጣሊያን በአፍሪካ አገራት የኢነርጂ ዘርፉ ላይ የጀመረችውን በጎ ስራ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠው ያሉትን ዕድሎች ወደ ሃብት ለመቀየርና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ዝግጁ መሆኗንም ነው ቋሚ ተወካዩ የተናገሩት።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ፣ በኢትዮጵያ ለኢነርጂ ኢንቨስትመንት መስክ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡  


 

የኢነርጂ ፖሊሲ ተከልሶ ወደ ትግበራ ለመግባት በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸው፤ ፖሊሲው የግል ዘርፉ ወደ ኢነርጂ ኢንቨስትመንት እንዲሰማራ የሚጋብዝ ነው ብለዋል፡፡  

የኢንቨስትመንት አዋጅ መሻሻሉም በኢነርጂ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰማሩ የግሉ ክፍል ኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ትልቅ ዕድል መሆኑን አመልክተዋል።

በኃይል ልማት እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ዙሪያ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ በጋራ መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረው ይህ ጉባኤም ለኢትዮጵያ ጥሩ አጋጣሚ ነው መሆኑንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያመለከቱት።

የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ መሻሻልም የግሉ ዘርፍ ወደ ኢነርጂ ኢንቨስትመንት እንዲገባ መንገድ የሚከፍት ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ አገራት የኤሌትሪክ ኃይል እየሸጠች እንደምትገኝና በኃይል ሽያጭ ምቹ ስትራጂቴካዊ አካባቢ ላይ እንደተቀመጠች አመልክተዋል፡፡ 

ለሶስት ቀናት በሚቆየው የፖሊሲ ምክክር መድረክ በአፍሪካ የኃይል ልማት ላይ የተሰሩ ጥናቶች ቀርበው በመንግስትና የግል ዘርፍ ኃላፊዎች ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም