የኢትዮጵያ የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽን የምክክር አገልግሎት ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆነ 

292

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2015  (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽን የምክክር አገልግሎት ፍኖተ ካርታ ዛሬ ይፋ ሆኗል። 

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ለቀጣይ ሰባት ዓመታት ስራ ላይ እንደሚውል ተገልጿል።   

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ እንዳሉት፤ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና የኤክስቴንሽን አገልግሎት መጠናከር አለበት። 

በተለይም ደግሞ የተቀናጀ የዲጂታል ኤክስቴንሽን አገልግሎት ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑንና ይህን ታሳቢ ያደረገ ፍኖተ ካርታው መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ፍኖተ ካርታው የኤክስቴንሽን አገልግሎቱን በወጥነት ለመምራት እንደሚያስችልና በተለያዩ ተቋማት የሚሰራውን የግብርና ዲጂታል ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለማቀናጀት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በፍኖተ ካርታው አማካኝነት የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አማራጮችና ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ወቅታዊ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና ምክር ለአርሶና አርብቶ አደሩ ይሰጣል ነው ያሉት።

አርሶ አደሩ የምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና የፀረ አረም ኬሚካልን በመጠቀም አርሶ አደሩ ገበያ ተኮር ምርት እንዲያመርት የሚያስችሉ የመረጃ ልውውጥ ይደረጋል ብለዋል።

ፍኖተ ካርታው የግብርና ኤክስቴንሽን የምክር አገልግሎት ዘመናዊ በማድረግ በቂ መረጃ ለአርሶ አደሩ በመስጠት ምርትና ምርታነትን ለማሳደግ ያስችላል ያሉት ደግሞ የግብርና ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር መለሰ መኮንን ናቸው።

የግብርናውን ዘርፍ አሁን ካለበት በማዘመን በአገር ደረጃ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በሁሉም የግብርና ዘርፎች እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩን በእውቅትና በክህሎት በማብቃት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ዛሬ ይፋ የሆነው ፍኖተ ካርታም የዚህ ጥረት አንዱ ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም