ፋብሪካው የሚያቀርበው ዳቦ በዋጋም ሆነ በጥራት የህብረተሰቡን አቅምና ፍላጎት ያገናዘበ ነው- ተጠቃሚዎች

ጎንደር፤  19 ቀን 2015(ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ተገንብቶ በቅርቡ ሥራ የጀመረው የዱቄትና ዳቦ ፋብሪካ የሚያቀርበው ዳቦ በዋጋም ሆነ በመጠን የህብረተሰቡን  አቅም ያገናዘበ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተጠቃሚዎች ተናገሩ፡፡

በከተማው ዳቦ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ 15 የዳቦ መሸጫ ሱቆች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አስታውቀዋል።

በከተማው የቀበሌ 09 ነዋሪው አቶ ካሳሁን ምትኩ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤  በፋብሪካው የሚመረተው ዳቦ በመጠንም  ሆነ በዋጋ  እሳቸውን ጨምሮ ሌላውንም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል አቅምን ያገናዘበ በመሆኑ ተመራጭ ነው። 

አንድ ዳቦ ከግል የዳቦ መሸጫ ሱቅ ከስምንት እስከ ሰባት ብር እየገዙ ሲጠቀሙ መቆየታቸውን ያስታወሱት አስተያየት ሰጪው፤ አሁን በፋብሪካ የሚቀርበው ዳቦ የሦስት ብር ቅናሽ እንዳለው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡

ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት አዲሱ እሸቴ ፤ በአካባቢው የዳቦ ዋጋ በየጊዜው ጭማሪ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፤ ፋብሪካው የሚያቀርበው ዳቦ በመጠንም ሆነ በጥራት የተጠቃሚውን ፍላጎት እንደማያሟላ ገልጿል፡፡

በፋብሪካው የሚመረተውን ዳቦ ከግል ዳቦ መሸጫ ሱቆች በዋጋና በመጠን የተሻለ በመሆኑ በአራት ብር ሂሳብ  በመግዛት እየተጠቀመ እንደሆነ ተናግሯል።

በግል ዳቦ ቤቶች በመጠን ያነሰና አንዱ ዳቦ ስምንት ብር እንደሚሸጥ ጠቁሟል፡፡

ከግል ዳቦ ቤቶች የሚሸጠው ዳቦ መጠኑ አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ዋጋውም የተጋነነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በከተማው የቀበሌ 03 ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉ ጀንበር ናቸው፡፡

በፋብሪካው እየቀረበ ያለው ዳቦ የዋጋ ቅናሽ ያለው ፤  ክብደቱም ሆነ ጥራቱ ተመራጭ በመሆኑም ስርጭቱ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በከተማው የቀበሌ 05 ነዋሪ  ወይዘሪት እናት ማሪቱ ፤ በከተማዋ የዳቦ መሸጫ ሱቆች መከፈታቸው የሥራ እድል እንደፈጠረላቸው ተናግራለች። 

የጎንደር ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አለምነው በበኩላቸው ፤ፋብሪካው የሚያመርተውን ዳቦ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ 15 መሸጫ ሱቆች መቋቋማቸውን አስታውቀዋል።

የአንዱ ዳቦ ክብደት 100 ግራም እንዲሆንና በአራት ብር ሂሳብ እንዲሸጥ የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡

በገቢና በኑሮ ዝቅተኛ የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ የተቋቋመው ፋብሪካ በቀጣይ የዳቦ ስርጭቱ ባልተዳረሰባቸው የከተማው ክፍሎች፣ አጎራባች ወረዳዎችና ሌሎች ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

ፋብሪካው 40 ለሚደርሱ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ እድል መፍጠሩን የተናገሩት አቶ መስፍን፤ በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት ሲሸጋገር በቀን 300 ሺህ ዳቦ የማምረት አቅም አለው ብለዋል፡፡

በቀን 450 ኩንታል የስንዴ ዱቄት የማምረት አቅም ያለው የዱቁት ፋብሪካው ከዳቦ ማምረቻው ጋር አብሮ እንደተቋቋመ አውሰተው፤  ፋብሪካው የስንዴ ግብዓት ከገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን እየቀረበለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

የጎንደር ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ የተቋቋመ ሲሆን፣ ባለፈው ወር በቀዳማዊት ዝናሽ ታያቸው ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱ  ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም