ኢንተርፕራይዞች በመንግስት ዋስትና ብድር የሚያገኙበት ስርዓት እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢንተርፕራይዞች በመንግስት ዋስትና ብድር የሚያገኙበት ስርዓት እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2015 (ኢዜአ)፦ኢንተርፕራይዞች በመንግስት ዋስትና ብድር የሚያገኙበት ስርዓት እየተዘጋጀ መሆኑን የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ።
ኢንተርፕራይዞች ከምሥረታቸው ጀምሮ በእንቅስቃሴ ሂደታቸው የፋይናንስ፣ የመሥሪያና መሸጫ ቦታዎች እንዲሁም የገበያ ትስስር ፈተናዎች እንደሚገጥማቸው በተደጋጋሚ ይነሳል።
ኢንተርፕይዞች ሰፍተውና ጎልብተው የሥራ ዕድል እንዳይፈጥሩ የፋይናንስ አቅርቦት ዋነኛ ማነቆ እንደሆነ እንዲሁ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ ክፍተት፣ የብድር ዋስትናና አማራጭ የሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል።
ምክክሩን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከፈርስት ኮንሰልትና ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በትብበር የተዘጋጀ ነው።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በዚሁ ወቅት እንዳሉት የብድር ዋስትና በኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ለሆኑት ለጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ወሳኝ ነው።
ኢንተርፕራይዞችን ከተመሠረቱ በኋላም ብድር ለማግኘት በመንግሥት ዋስትና ከአበዳሪ ተቋማት ብድር የሚያገኙበት ሥርዓት እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።
የብድር ዋስትናው የኢንተርፕራይዞች ዕድገት በማረጋግጥ ውጤታማ ስለሚያደርጋቸው በመንግሥት ዋስትና የሚወሰደው ገንዘብ እንደማያከስር ታምኖበታል ብለዋል።
የብድርና የመሬት አቅርቦት እንዲሁም የገበያ ትስስር ተግዳሮት በሆነበት ስኬታማ ኢንተርፕራይዞችን ማፍራትና የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ማድረግ አዳጋች መሆኑን ጠቁመዋል።
የብድር ዋስትና ሥርዓት መዘርጋቱ ኢንተርፕራይዞች ብድር ለማግኘት የሚገጥማቸውን የዋስትና ችግር በመፍታት ምርታማ እንደሚያደርጋቸውም ጠቁመዋል።
በኢኮኖሚው ውስጥ የተሻለ ሚና እንዲኖራቸውም ያደርጋል ብለዋል።
በጥናት በቀረቡ አማራጮች ላይ በቀጣይ ባለሙያዎች፣ አጋር አካላትና የፋይናንስ ተቋማት መክረውበት ከዳበረ በኋላ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ የብድር ዋስትና ፈንድ እንደሚቋቋም ገልጸዋል።
የፋይናንስ አቅርቦቱና የድጋፍ አገልግሎቱን አጣጥሞ ከተሰራበት የኢንተርፕራይዞች የመክሰም ምጣኔ እየቀነሰ እንደሚሄድ አቶ ንጉሡ አመላክተዋል።
ኢንተርፕራይዞቹ ውጤታማ እንዲሆኑና እንዳይከስሩ እንዲሁም አበዳሪ ተቋማትንም ይዘው እንዳይወድቁ መንግሥት በኃላፊነት ብቃታቸውን የማሳደግና አቅማቸውን የማጎልበት ሥራ እንደሚሰራ አስረድተዋል።