የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከኩዮቶ ዩኒቨርሲቲየቲ የተሽከርካሪዎች ድጋፍ አገኘ

ጂንካ፣ መጋቢት 19 / 2015 (ኢዜአ) የጃፓኑ ኩዮቶ ዩኒቨርሲቲ ለጂንካ ዩኒቨርሲቲ 20 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሁለት ተሽከርካሪዎች ዛሬ በድጋፍ አበረከተ።

ድጋፉን የኩዮቶ ዩኒቨርሲቲ ተወካይና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሻጊታ ማሳዮ ለጂንካ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኤሊያስ አለሙ አስረክበዋል።

ዶክተር ኤሊያስ  ለተደረገው ድጋፍ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ድጋፉ ዩኒቨርሲቲው ያለበትን የተሽከርካሪዎች እጥረት በማቃል  ለጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለማሳለጥና በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች ለመንቀሳቀስ  የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

የጃፓን መንግስት ከሚያደርገው የቁሳቁስ ድጋፍ ባሻገር በጥናትና ምርምር ሥራዎች ከዩኒቨርስቲው ጋር በመሥራትና ልምድ በማካፈል ድጋፍ በማድረግ  ላይ እንደሚገኝ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ሻጊታ በበኩላቸው፤ ድጋፉ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያከናውናቸውን የጥናትና ምርምር ሥራዎች ለማሳደግ እገዛውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ትብብር እንደሚያደርግ  ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የጃፓን መንግስት በሦስት ሚሊዮን ብር ወጪ ዘርፈ-ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ የስልጠና ማዕከል ለዩኒቨርስቲው በመገንባት የላብራቶሪ ቁሳቁሶችን ማበርከቱን አስታውሰዋል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የብዝሀ-ባህል፣ ብዝሀ ህይወት፣ እንስሳትና ዓሣ ሀብት፣ የግብርናና መሰል የትኩረት መስኮች ላይ የልህቀት ማዕከል ሆኖ አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አለሙ አይሌቴ  ናቸው።

የጃፓን መንግሥት እያደረገ ያለው ድጋፍ ዩኒቨርሲቲው በልህቀት ማዕከልነት ለሚያከናውናቸው የትኩረት መስኮች መሳካት አጋዥ እንደሆነ ተናግረዋል።

የጃፓን መንግስት በተለይ በጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር (ጃይካ) አማካይነት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የልማት ፕሮጀክቶች በመቅረፅ ድጋፍ ገቢራዊ እያደረገ እንደሆነ በወቅቱ ተናግረዋል።

ከፕሮጀክቶቹ በመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ ረገድ በአፈር ጥናት ላይ ከአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጣምራ እየሰራ ሲሆን፣ በአነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታና ጥገና አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱ ተመልክቷል።

በአሁኑ ወቅትም አህጉራዊ፣ አገራዊና አለም አቀፋዊ ትስስር ያለው የጥናትና ምርምር ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ላይ እንደሚገኝ ተወስቷል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም