ኢትዮጵያና ላቲቪያ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2015(ኢዜአ) ኢትዮጵያና ላቲቪያ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመስራት መስማማታቸው ተገልጿል

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ከላቲቪያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስተር የፖለቲካ ዳይሬክተር ቢሮ ረዳት ዋና ፀሐፊ አንዜጂስ ቫይሉምሰንስ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ ሁለቱ አገራት በሁለትዮሽና በባለ ብዙ ወገን የትብብር መስኮች ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር ላይ ያተኮረ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

አምባሳደር እሸቴ ለቫይሉምሰንስ ስለ ሰላም ሂደቱ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ላቲቪያ በአውሮፓ ሕብረትና ባልቲክ ባህር ቀጠና ወሳኝ ሚና የምትወጣ አገር ናትብለዋል።

ኢትዮጵያና ላቲቪያ ያላቸውን ግንኙነት ለማሳደግ ተቀራርበው መስራት እንደሚኖርባቸውም ነው አምባሳደሩ ያመለከቱት።

ሁለቱ አገራት በውሃ ሀብት አስተዳደር፣ በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት፣ ትምህርት፣ ኢንፎርሜሽና ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎሎጂ፣ በግብርና፣ በቱሪዝምና ሌሎች ቁልፍ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል፣ ሰላምና ደህንነት፣ በስደተኞችና ሌሎች የጋራ ጠቀሜታ ባላቸው ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በቅርበት ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆኑ መግለጻቸውም ተገልጿል።

ኢትዮጵያና ላቲቪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት .. 2008 ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም