30 ባለማቀዝቀዣ ኮንቴይነሮች ግዢ ተፈጽሞ እየተጓጓዙ ነው- የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት - ኢዜአ አማርኛ
30 ባለማቀዝቀዣ ኮንቴይነሮች ግዢ ተፈጽሞ እየተጓጓዙ ነው- የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት
አዲስ አበባ መጋቢት 19/2015 (ኢዜአ)፦ ሰላሳ ባለማቀዝቀዣ ኮንቴይነሮች ግዢ ተፈጽሞ ወደ ጅቡቲ ወደብ እየተጓጓዙ መሆኑን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።
ባለማቀዝቀዣ ኮንቴይነሮቹ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ጥራታቸው እንደተጠበቀ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችሉ መሆናቸውም ተገልጿል።
ኮንቴይነሮቹ በመጪው ሳምንት ጅቡቲ ወደብ እንደሚደርሱም ከድርጅቱ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
ባለ ማቀዝቀዣ ኮንቴይነሮቹን ማስተናገድ የሚችል ልዩ ተርሚናል በሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል መዘጋጀቱን ተገልጿል።
ኮንቴይነሮቹ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡና በቀላሉ ሊበላሹ የሚችሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ባሉበት ሁኔታ ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ መዳረሻቸው እንዲጓጓዙ ለማድረግ እንደሚያስችሉም ተጠቅሷል።
የወጪ ምርቶችን በባቡር እና በመርከብ በፍጥነት በማጓጓዝ ወደ መዳረሻቸው ለማድረስ እንዲሁም የወጪ ንግድን በመደገፍና በማሳደግ ረገድ ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው ተመላክቷል።