በደቡብ ኦሞ ዞን ባህላዊውን የዋና ስፖርትን ለማዘመን ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ገለጸ

528

ጂንካ መጋቢት 19 / 2015 (ኢዜአ) በደቡብ ኦሞ ዞን የሚዘወተረውን ባህላዊ የውሃ ዋና ስፖርት በማዘመን በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑ ስፖርተኞችን ለማፍራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ገለጸ።
በኦሞ ተፋሰስ አካባቢ የሚገኙ አርብቶ አደሮች የዕለት ተዕለት መስተጋብር ውጤት የሆነው የውሃ ዋና ስፖርት በአካባቢው ከልጅነት እድሜ ጀምሮ ይዘወተራል።

ስፖርቱን ለማበረታታት ያለመ የውሃ ዋና ስፖርት ውድድር በኦሞራቴ ከተማ አቅራቢያ በመምሪያው አዘጋጅነት ዛሬ ተካሂዷል።

ይህን ባህላዊ የውሃ ዋና ስፖርት ላይ ዘመናዊ ዕውቀቶችን እና ክህሎቶችን መጨመርና ማከል ቢቻል ከአገር አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በመሆን የአገሪቱን ስም የሚያስጠሩ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚቻል ተገልጿል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ወሊ ኃይሌ እንደተናገሩት፤ በኦሞ ወንዝ ላይ በርካቶች እንደ ባህል አድርገው የዋና ስፖርትን ያዘወትራሉ።

ከዚህ ልምድ ተነስቶ የዘወትር ተግባር እየሆነ የመጣው የውሃ ዋና ስፖርት ማሳደግ ቢቻል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪና ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ ተተኪ ስፖርተኞች ማፍራት የሚያስችል ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት አመታት በዞኑ በውሃ ዋና ስፖርት ላይ በልዩ ትኩረት በተሰሩ ስራዎች ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸው፤ ከአገር ውስጥ አልፎ በውጭ አገራት ተወዳዳሪ የሆኑ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደተቻለ ተናግረዋል።

ይህን በማስፋት በተለይ በኦሞ ወንዝ ዳርቻ የሚገኙ ባህላዊ የውሃ ዋናተኞች ላይ በትኩረት ቢሰራ በርካታ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚቻል ገልፀዋል።

ያለውን የውሃ ዋና ስፖርት እምቅ አቅም ለማሳደግ ውድድሮችን ማካሄድና ሁኔታዎች በማመቻቸት ትኩረት እንዲሰጠው እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ስፖርቱን ውጤታማ ለማድረግ የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በአሁኑ ሰአት ስፖርተኞቹ በወራጅ ወንዞች ላይ ልምምድ እያደረጉ በመሆናቸው ሳይንሳዊ የውሃ ዋና ቴክኒኮችን ለማስተማር ተግዳሮት እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል።

በመሆኑም ዘመናዊ የመዋኛ ገንዳ፣ የመዋኛ አልባሳት እና የመሳሰሉ ግብአቶችን በማሟላት ረገድ የክልሉና የፌዴራል የውሃ ዋና ፌዴሬሽኖች እገዛ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

በመምሪያው የስፖርት ዘርፍ የስፖርት ውድድር እና ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ አስራት ጊዮርጊስ በበኩላቸው በኦሞ ተፋሰስ አካባቢ ያለውን የውሃ ዋና ስፖርት እምቅ አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ባህላዊው የውሃ ዋና ስፖርት ወደ ዘመናዊነት ማሳደግ ቢቻል በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚቻል ተናግረዋል ።

የውሃ ዋና ስፖርት በጣም የሚወደው ስፖርት እንደሆነ የሚናገረው የኦሞራቴ ከተማ ነዋሪው ወጣት በለዋ ሎንጋርቾ፤ የዋና ስፖርት የሚያከናውኑበት የኦሞ ወንዝ የውሃ ዋና ቴክኒኮችን ለመለማመድ እንደማያስችላቸው ገልጿል።

በቀጣይ መዋኛ ገንዳዎች ቢሰሩ፣ የተለያዩ ቴክኒኮችን የሚያስተምሩ አሰልጣኞች ቢሟሉና ሌሎች ድጋፎች ቢደረጉልን በስፖርቱ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንችላለን ሲል ለኢዜአ ገልጿል።

በአካባቢው የሚገኙ ስፖርተኞችን ለማበረታት በዳሰነች ወረዳ ኦሞራቴ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው በኦሞ ወንዝ ላይ የውሃ ዋና ስፖርታዊ ውድድር የተካሄደ ሲሆን በሁለቱም ፆታዎች አሸናፊ ለሆኑ ስፖርተኞች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም