በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ግጭቶችን በመከላከል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በጋራ መሥራት ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ 

 አዲስ አበባ መጋቢት 19/2015  (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችን በመከላከል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በጋራ መሥራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ። 

በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ የምክር ቤት አባላት ላነሱት ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ምላሽ ሰጥተዋል።

በዚህም በምዕራብ ወለጋ አካባቢ የሸኔ ታጣቂ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በሰላም ለመፍታት መንግሥት የሄደበትን እርቀት በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ባለፉት አምስት ዓመታት በወለጋ አካባቢ የተፈጠረው የሰላም እጦት የልማት ሥራዎችን ለመሥራት እንቅፋት ከመሆን ባለፈ ለሰዎች መሞት፣ መፈናቀልና መሰደድ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። 

በአካባቢው የተፈጠረውን የሰላም እጦት ወደ ነበረበት ለመመለስ መንግሥት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ፤ ለዚህ ይረዳ ዘንድ የሰላም ኮሚቴ በማቋቋም እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

ችግሩን ለመፍታት ባለፉት ሁለት ወራት በመንግሥት በኩል ከአሥር ጊዜ በላይ ሙከራዎች ቢደረጉም በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት ታጣቂ ኃይሎች አሰላለፍ የተበታተነ በመሆኑ ሂደቱን አዳጋች እንዳደረገው ጠቁመዋል።

"ሰላምን የሚጠላ ኃይል የለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለስኬቱ አበክረን እንሰራለን በማለት የመንግሥትን አቋም ግልጽ አድርገዋል።

ነገር ግን ለሰላም ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር የተጠናከረ ሥራ እየሰሩ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።

"መገዳደል ለማንም አይጠቅምም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ችግሮችን በውይይት መፍታት ጠቃሚ ነው ብለዋል።

የሰላም ሂደቱን በተመለከተ ውጤቱን በጋራ የምናየው ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል። 

በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት መቆሙ አንድ እርምጃ ወደፊት ወስዶናል፤ ነገር ግን ወደተሟላ ሰላም ለመሄድ በርካታ ሥራዎች ይጠብቁናል በማለት ገልጸዋል። 

ግጭቶች የአገሪቱን ዕድገት ወደ ኋላ እየጎተቱ በመሆኑ ለሰላም መስፈን በጋራ መሥራት አለብን ሲሉ አሳስበዋል። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም