የዋጋ ንረትን ለመቀነስ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው--ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

235

 

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2015 (ኢዜአ)፦ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ በመንግስት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተለያዩ ጉዳዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ እየሰጡ ይገኛሉ። 
 
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የዋጋ ግሽበት ጉዳይን የተመለከተ ነው።   

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በምላሽ እና ማብራሪያቸው የዋጋ ግሽበቱን ለመቀነስ በመንግስት እየተተገበሩ የሚገኙ ስራዎችን ዘርዝረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ያጋጠመው የዋጋ ንረት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች እየጎዳ መሆኑን መንግስት በጽኑ ይገነዘባል ብለዋል።

አሁን ላይ የታየው የዋጋ ንረት ችግር ላለፉት 20 ዓመታት የማያቋርጥ የዋጋ ንረት መፈጠሩ አንዱ ምክንያት  መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሸማች እና አምራች መካከል ያለውን ክፍተት ማስተካከል ካለመቻሉም በላይ  ጦርነት፣ ድርቅ፣ የአጋር አካላት እርዳታ መቀነስ እና ወደ ከተማ ፍልሰት መጨመር ለዋጋ ንረቱ መፈጠር ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው ሲሉም አክለዋል።

የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ እየተተገበሩ የሚገኙ መፍትሄዎች የምርት አቅርቦት ላይ በስፋት መስራት፣ የምገባ ማእከል እና የማዕድ ማጋራት ስርዓትን ማስፋት ላይ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ 

የዋጋ ንረቱን መቀነስ የሚያስችል የተለያዩ ደጎማዎች እየተደረጉ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሳያነትም በነዳጅ ላይ ባለፉት 8 ወራት ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ መደጎሙን ጠቅሰዋል፡፡ 

በዚህም 133 ሺህ ገደማ የሚሆኑ ተሸከርካሪዎች የድጎማው ተጠቃሚ ሆነዋል ነው ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም