ድንበር አካባቢ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ በንግግር መፍታት ኢትዮጵያ ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ ነው--ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2015 (ኢዜአ) ድንበር አካባቢ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ በንግግር መፍታት ኢትዮጵያ ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ  ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተለያዩ ጉዳዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ እየሰጡ ይገኛሉ

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ኢትዮጵያ ከሱዳንና ደቡብ ሱዳን ከምትዋሰንበት ድንበሮች ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ችግሮችን የተመለከተ ነው።  

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ድንበር አካባቢዎች ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ለውይይትና ሠላማዊ መንገድ ቅድሚያ መሰጠቱን አስረድተዋል።  

ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በሚያዋስናት ድንበር ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ኮሚሽን ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።    

ከሱዳን ጋር ያለው ችግር በዘላቂነት የሚፈታው ድንበር የማካለሉ ጉዳይ እልባት ሲያገኝ መሆኑን ገልጸው እስከዛው ግለሰቦችና አርሶ አደሮች እንዳይጉላሉ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ጎን ለጎንም "የደቡብ ሱዳን መንግሥት ኢትዮጵያን ወሯል በሚል የሚነሳው አገላለጽ ትክክል አይደለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደቡብ ሱዳን አርሶና አርብቶ አደሮች ድርቅ ገጥሞናል በሚል 20ሺህ ያህል ከብቶችን ነድተው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አልፈው መግባታቸውን አንስተዋል።

ይህንንም በተመለከተ "ከአርሶና አርብቶ አደሩ ጋር ንግግር ተደርጓል፤ የሚያሰጋ ነገር አይፈጠርም" ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያረጋገጡት።  

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ከደቡብ ሱዳን ድንበር ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን ችግር በሁለቱ አገራት መካከል ውይይት በማድረግ ችግሩን ለመፍታት ከመግባባት ላይ ተደርሷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም